All about Tedy Afro

 

Ethiopia Zare (ኀሙስ መስከረም ፳፱-29 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 9, 2008)፦ ዛሬ ኀሙስ መስከረም 29 እንደተለመደው በጠዋቱ ችሎት ጉዳዩ ይታያል ብሎ የገመተ ቁጥሩን ለመገመት የሚያዳግት በርካታ ችሎት ተከታታይ ገና ከጠዋቱ ነበር፣ የፌደራሉ ፍርድ ቤት ሁለቱ መግቢያዎች ላይ እየተጋፋ የተሰለፈው።

 

ነገር ግን በችሎቱ መግቢያ ላይ ያልተለመደ ነገር ጎድሎ ነበር፤ ታዋቂውና ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን የሚመጣባት የፖሊስ ነጭ ሚኒባስና በርካታ ፌደራል ፖሊሶች አልነበሩም። ጉዳዩን የተጠራጠሩ በያለበት ደወሉ፤ ችሎቱ ለሁለት ሲከፈል ሙሉ ቁጥር ያላቸው መዝገቦች የሚታዩት በከሰዓት በኋላ ችሎት ነው ተባለ። አንዳንዱ ከሰልፉ እየወጣ ወደመጣበት ሲመለስ፣ አብዛኛው ግን እዚያው ችሎት ለመቆየት ወሰነ።

 

በተለመደው የከሰዓቱ የፍርድ ቤት መግቢያ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ለመግባት እስኪፈቀድልን ተረጋግተን መግቢያ በር ላይ ቆመናል። ሰዓቱ ሲደርስም በተጠየቅነው መሠረት መታወቂያችንን እያሳየን ወደ ውስጥ ዘለቅን። ችሎቱ መግቢያ ላይ ስንደርስ ግን ችሎቱ በመሙላቱ ለአምስት ሰዎዎች ብቻ ተባለ። ባደረግነው ጠንካራ የሩጫ ፉክክር የመጨረሻዎቹ አምስት ሰዎዎች ሆንን፤ ለካ ቀኑን ሙሉ እዚያው የዋለው አብዛኛው ተመልካች ችሎቱን ሞልቶት ነበር።

 

ችሎት ተከታታዩን ብዙም ሳያስጠብቅ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ የተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐብሔር ችሎት ከአቶ ልዑል ገ/ማርያም ቀደም ብለው፣ ይህንኑ የወንጀል ችሎት ያስችሉ በነበሩትና ትናንት በተሰየሙት አዲስ ዳኛ መሐመድ ዑመር ችሎቱ ሥራውን ጀመረ።

 

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ከጠበቆቹ አቶ ሚሊዮን አሰፋና አቶ አመኀ በድሉ ጋር፣ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ፀጋ መቅረባቸው ከተረጋገጠ በኋላ መዝገቡ የተቀጠረው፣ የተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሣሁንን የመከላከያ ምስክሮች ለመስማት በመሆኑ ምስክሮች መቅረባቸው ይረጋገጥ ተባለ።

 

የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን ከቆጠሯቸው 14 ምስክሮች ለ12ቱ መጥሪያ ማድረሳቸው፣ ከነዚህም ሁለቱን ያላገኟቸው መሆኑንና ስለሁለቱ ምስክሮች መጨረሻ ላይ ሃሳባቸውን እንደሚያስመዘግቡ በመግለጽ ምስክሮቻቸው የሚመሰክሩትን ጭብጥ ለማስያዝ ጠየቁ።

 

ዓቃቤ ሕግ “ተቃውሞ አለኝ” ሲል ተቃውሞውን አቀረበ። ምስክሮቹ ተሟልተው ባልቀረቡበት ሁኔታ የቀረቡ ምስክሮች ምስክርነት ሊሰማ አይገባም። የተከሳሽ የጽሑፍ ማስረጃና ምስክሮቹ የሚያስረዱት ጭብጥ እዚሁ የቀረበልን በመሆኑ፣ ባልተዘጋጀንበት ሁኔታ ጥያቄዎችን ማቅረብ የሚያስቸግረን በመሆኑና በተከላካይ ምስክርነት የቀረቡት የኩባ ዜግነት ያላቸው የምኒልክ ሆስፒታል የአስከሬን መርማሪ አስተርጓሚዎች፣ በተከሳሾቹ የቀረቡ በመሆናቸው እንደማይተማመኑና ፍርድ ቤቱ ሌላ አስተርጓሚ እንዲሾምላቸው ጠየቁ።

 

ፍርድ ቤቱም ምስክሮቹ የሚያስረዱት ጭብጥም ሆነ የሰነድ ማስረጃ፣ ተከሳሽ ለፍርድ ቤቱ በጊዜው አቅርቦ ከመዝገቡ ጋር ተያይዟል፣ ምስክሮችንም በሚመለከት ያቀረባችሁት አቤቱታዎች ምስክር እንዳይሰማ በሚያግድ ሁኔታ በሕግ የተደገፈ ባለመሆኑ አቤቱታችሁ ተቀባይነት አላገኘም። አስተርጓሚዎቹን በሚመለከት ደግሞ ፍርድ ቤት እስከ ዛሬ ባለው አሠራር አስተርጓሚ የሚሾመውና ያጋጠመው እንግሊዘኛ ተናጋሪዎችን ነው። እንዲህ ዓይነት በሌላ ቋንቋ የሚናገር ምስክር ሲገጥመው ምናልባት የቀረቡት አስተርጓሚዎች፣ ከተከሳሽ ጋር ዝምድና የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጦና መሐላ ፈጽመው የሚመሰክሩበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚችልና ለማንኛውም ሃሳባቸውን መጨረሻ ላይ ማመልከት እንደሚችሉ በመግለጽ ችሎቱ ሥራውን ጀመረ።

 

የቴዎድሮስ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ፣ ምስክሮቹ ምን እንደሚያስረዱ ጭብጥ ያስያዙ ሲሆን፣ በጭብጡም ሦስቱ ምስክሮች ተከሳሹ አቶ ቴዎድሮስ ካሣሁን ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ጠዋት ከካናዳ አዲስ አበባ ከገባበት ሰዓት ጀምሮ፣ ከአውሮፕላን ማረፊያ የተቀበሉትን፣ አብረው ምሳ የበሉትን፣ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓትና እስከ ለሊቱ 9 ሰዓት ድረስ አብረውት የነበሩትን፣ ሦስት ምስክሮች ምን እንደሚያስረዱለት በዝርዝር አቅርበዋል።

 

ለተከሳሽ የእስር ምክንያት የሆነው የሟች አስከሬን በጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ምኒልክ ሆስፒታል ገብቶ፣ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. የአስከሬን ምርመራ እንደተደረገለት የሚገልጸውን የሰነድ ማስረጃ የሰጡት የምኒልክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ስለሰነድ አሰጣጡና ሰነዱ በሆስፒታሉ ስለሚቀየርበት ሁኔታ፣ ይህንኑ ማስረጃ የሟች አስከሬን በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ምኒልክ ሆስፒታል ገብቶ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. የአስከሬን ምርመራ እንደተደረገለት የሚገልጽ ማስረጃ ላይ ሥምና ማኅተማቸውን ያሳረፉትን የምኒልክ ሆስፒታል ኩባዊው የአስከሬን መርማሪ የተቀየረውን የአስከሬን ምርመራ ውጤት በሸኚ ደብዳቤ የላኩትን የምኒልክ ሆስፒታል ሠራተኛ፣ የተከሳሹ መኪና ግጭት ከደረሰባት ሲ.ኤም.ሲ. ተወስዳ፣ ተከሳሹ በሌለበትና ባልፈረመበት ሁኔታ የተሽከርካሪ ምርመራ አድርጎ ማስረጃ የሰጠውን ግለሰብ በምስክርነት መቁጠሩን እና ምን እንደሚያስረዱለት በጭብጡ አስይዟል።

 

ከጭብጡ በኋላ አምስት ምስክሮችና ሁለት አስተርጓሚዎች የክርስትና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው በእግዚአብሔር ስም ሲምሉ፣ ሁለቱ ሙስሊም በመሆናቸው በአላህ ስም ምለዋል።

 

የቴዲ የተከሳሽ የምስክርነት ቃል

ጠበቃው ከምስክሮቹ በፊት ቴዎድሮስ ካሣሁን የተከሳሽነት ቃል እንዲያሰማ ተጠይቆ በተፈቀደለት መሠረት ”በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባሁ። ምትኩ ግርማ የተባለው ጓደኛዬ ከማናጀሬ ቀጥሎ ጉዳዬን የሚፈጽምልኝ ሲሆን፣ በዕለቱ ከኤርፖርት ከተቀበለኝ በኋላ ሚኪስ ፋሽን የተባለ ልብስ ቤት ሄደን ልብስ ገዛሁ። ምሳ ከበላን በኋላ ወደ ያሲን ቤት ሄድኩ። ከዚያም እዚያ ውለን ወደ አራት ሰዓት አካባቢ ማምሻውን ከያሲን ቤት ወጥተን መስቀል ፍላወር አካባቢ ያለ ቤት አመሸን፣ በኋላ ሳምሶን የተባለ ጓደኛዬ መጥቶ ነበር። ከለሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ከዛ ወጣን፣ እኔና ሳምሶን ኦሎምፒያ ድረስ አብረን ሄድን፣ እኔ የማሲንቆ ጨዋታ እወድ ስለነበር ወደ ካሳንችስ ይወዳል ቤት እየነዳሁ ሄድኩ። እዚያ ከደረስኩ በኋላ ሃሳቤን ቀየርኩና ወደ ቤቴ ሲ.ኤም.ሲ መንገድ ጀመርኩ፣ ምንግዜም ከውጭ ስመጣ የሄድኩባቸው ሀገራትና የዚህ ሀገር የእንቅልፍ ሰዓት ለማስተካከል ስለሚከብደኝ ነበር ቀኑን ውጭ ያሳለፍኩት። እንደሚታወቀውና ሐኪምም እንደሚለው እንዲህ ዓይነት የእንቅልፍ መዛባት ሲገጥም መኪና መንዳት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ ላይ ውጭ በነበርኩበት ግዜ ተጀምሮ በምኖርበት ሲ.ኤም.ሲ. አካባቢ የመንገድ ኮንስትራክሽን ሥራ ተጀምሮ ስለነበር አባጣና ጎርባጣውን መንገድ አላየሁትም ነበርና ከለሊቱ 9 ሰዓት አካባበቢ ከግዑዝ ነገር ጋር ተጋጨሁ። በሰዓቱ ብዙ ነገሮችን ወደሚረዳኝ ምትኩ ጋር ደወልኩ፣ ስልኩን ሊያነሳልኝ አልቻለም። መኪናዬ ውስጥ ያሉትን ካሴቶቼንና ወረቀቶቼን ሰብስቤ በላስቲክ ካደረኩ በኋላ ሠፈራችን ያለ የፔፕሲ ሠራተኛ አግኝቶኝ በመኪናው ወደ ቤቱ ወሰደኝ። ጠዋት ምትኩ የደወልኩለትን ስልክ አይቶ ደወለለኝ። የደረሰብኝን ነገርኩትና መኪናዋ መንገድ ዘግታ ስለቆመች እንዲያስጎትትልኝ ነገርኩት። በኋላ ላይ መኪናው በትራፊክ ጽሕፈት ቤት ሲያልፍ ታርጋ የለውም ተብሎ መታሠሩን ሰማሁ። ሌላ አንድ ላስገነዝብ የምፈልገው ነገር እኔ ሀገር ውስጥ የገባሁት በጥቅምት 23 ቀን ነው፣ የምኒልክ ሆስፒታል ማስረጃ እንደሚያስረዳው ደግሞ ሟች የሞተው በጥቅምት 22 ቀን ነው።” ሲል የተከሳሽነት ቃሉን ሰጠ።

 

ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ የሰጠው የተከሳሽነት ቃል ግልጽ በመሆኑ ማብራሪያ አያስፈልገውም ሲል የምስክሮችን ቃል ማድመጥ ጀምሯል።

 

የዶ/ር እርዳው አሻግሬ (የቀድሞው የምኒልክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር) ምስክርነት

የመጀመሪያ ምስክር ሆነው የቀረቡት የቀድሞ የምኒልክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር እርዳው አሻግሬ ሲሆኑ፣ ተከሳሹን በሞያቸው በድምፅና በቴሌቭዥን ከሚያዩዋቸው በስተቀር እንደማያውቋቸው ገልጸው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

 

ዶ/ር እርዳው የሟች ደጉ የአስከሬን ምርምራ ውጤት እንዲያዩት ከተደረገ በኋላ በሰጡት ምስክርነት፣ የምኒልክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የተጠቀሰውን ማስረጃ በስማቸውና በፊርማቸው ማኅተም አድርገው ሰጥተዋል። ይህንንም ከጠበቃው በሚቀርብላቸው ጥያቄ ሲያረጋግጡ ሟች ደጉ ይበልጣል አስከሬኑ ለምርመራ በጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ገብቶ፣ በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ምርመራ እንደተደረገለት የሚገልጸውን ማስረጃ ሲሰጡ፣ በወቅቱ ምርመራውን ያደረጉት ሐኪም ፈርመው ሲልኩላቸው ማስረጃው ትክክል መሆኑን አይተው አረጋግጠው ፊርማቸውን ማኖራቸውን ገልጸዋል።

 

”ማስረጃው ከቀሪው መዝገብ ጋር ተገናዝቦና በሚገባ ታይቶ የተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ በወቅቱ ምርመራውን ያደረጉት ሐኪም ከሀገር ይውጡ እንጂ የተጠቀሰው ቀን በማስረጃው ላይም ሆነ መዝገቡ ላይ አንድ ዓይነት ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰነዶችም ማንም ሊቀይራቸው እንደማይችል ገልጸው፣ ስህተት ቢያጋጥም እንኳ እንደ ፍርድ ቤት ያለ ሕጋዊ የሆነ አካል ሲጠይቅ፣ ስህተቱ የይዘት ለውጥ የማያመጣ ቀላል ከሆነና አሳማኝ የሆነ በቂ ምክንያት ካለው ሊስተካከል ይችላል።” ካሉ በኋላ እሳቸው የፈረሙበት ማስረጃ ከዋናው መዝገብ ጋር ተገናዝቦ የተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

 

የዶ/ር ካሣሁን አደም (በምኒልክ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት) ምስክርነት

ሌላው ምስክር በምኒልክ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና ሜዲካል ዳይሬክተሩ በሌሉ ግዜ ተወክዬ እሠራለሁ ያሉት ዶ/ር ካሣሁን አደም ሲሆኑ፣ ሟች ደጉ ይበልጣል አስከሬኑ ለምርመራ በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ገብቶ፣ በጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ምርመራ እንደተደረገለት የሚገልጸውን ማስረጃ ፈርመው የሰጡ ናቸው።

 

ከጠበቃው ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ የአስከሬን ምርመራውን ባደረጉት ሐኪምና በወቅቱ በነበሩት ሜዲካል ዳይሬክተር አማካኝነት የተሰጠን ማስረጃ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በምን ሥልጣንና በምን ማስረጃ እንደቀየሩ ሲጠየቁ ”… በወቅቱ ምርመራውን ያደረጉት ሐኪም፤ የሟች አስከሬን በጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ምኒልክ ሆስፒታል ገብቶ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. የአስከሬን ምርመራ እንደተደረገለት የሚገልጽ ማስረጃ ቢሰጡም፤ ሐኪሟ በወቅቱ መሳሳታቸውን በማረጋገጣችን ማስረጃውን አስተካክለን ሰጥተናል።” ብለዋል።

 

”ማስረጃውን ስታስተካክሉ መነሻችሁ ምን ነበር?” በሚል ከጠበቃው ለቀረበላቸው ጥያቄም ”መዝገቡ ላይ የሠፈረው አስከሬኑ የገባው በጥቅምት 22 ቢሆንም ፖሊስ አስከሬኑን እኛ ጋር ሲያመጣ የሞላው ፎርም ጥቅምት 23 የሚል መሆኑን አረጋግጠን ሰጥተናል” ብለዋል።

 

ነገር ግን በወቅቱ ምርመራውን ያደረጉት ሐኪም በሰጡት ማስረጃም ሆነ መዝገብ ላይ ባሰፈሩት ሰነድ ሟች አስከሬኑ ለምርመራ የገባው በጥቅምት 22 ቀን መሆኑን አረጋግጠዋል።

 

የአቶ አብርሃም (የምኒልክ ሆስፒታል አስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ) ምስክርነት

ለሁለተኛውና ለተስተካከለው ማስረጃ ሸኚ ደብዳቤ የጻፉት የሆስፒታሉ አስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ አብርሃም በሰኔ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ መቆጣጠሪያና ምርመራ መምሪያ ጽፈውና ፈርመው በላኩት ሸኚ ደብዳቤ ”… የሟች ደጉ ይበልጣል አስከሬን በጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ምኒልክ ሆስፒታል ገብቶ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. የአስከሬን ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ የላክንላችሁ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ማስተካከያ ተደርጎ እንዲላክላችሁ መጠየቃችሁ ይታወቃል። በመሆኑም ሟች ደጉ ይበልጣል በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ሕይወታቸው አልፎ በዕለቱ አስከሬናቸው ወደ አስከሬን ክፍል ገብቶ የአስከሬን ምርመራው ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. የተደረገላቸው መሆኑን እያረጋገጥን ስህተቱ የተከሰተው በወቅቱ የነበሩት የአስከሬን መርማሪ ባለሙያ ወደ ዋናው መዝገብ በሚያሰፍሩበት ወቅት በተከሰተ ግድፈት መሆኑን እየገለጽን፣ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።” ማለታቸውን ጠበቃው ጠቅሰው ይህ ፊርማና ማኅተም የሳቸው መሆኑን ከራሳቸው ካረጋጋጡ በኋላ ”… ስህተቱ የተከሰተው በወቅቱ የነበሩት የአስከሬን መርማሪ ባለሙያ ወደ ዋናው መዝገብ በሚያሰፍሩበት ወቅት በተከሰተ ግድፈት መሆኑን እየገለጽን …” ብለዋል እናንተ በምን አረጋገጣችሁ? ሲሉ ጠይቀዋቸዋል። ኃላፊውም ማረጋገጫቸው ፖሊስ አስከሬኑን ይዞ ሲመጣ የሞላው ፎርም መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢንስፔክተር መሐመድ ምስክርነት

ሌላው ምስክር ኢንስፔክተር መሐመድ የተባሉ ሲሆኑ፣ በወቅቱ ትራፊክ ጽ/ቤት ቆማ የነበረቸውን የተከሳሽ መኪና ከ15 ቀናት በኋላ ምርመራ አድርገው ”… መኪናዋ ፊት በር አካባቢ ሰው ገጭታ ከዚያም ሲ.ኤም.ሲ. ሄዳ ተጋጨች …” የሚል የምርመራ ውጤት ለመስጠት ማስረጃችሁ ምንድነው? በዚህ የምርመራ ውጤት ላይስ ተከሳሹ እንዲፈርም ለምን አልተደረገም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ”… መኪናዋን ግጭቱ በደረሰበት ቦታ አላገኘኋትም፣ መነሻውን ያገኘሁት ከመርማሪ ፖሊሱ ነው፣ መኪናዋ ላይ ምንም አይነት የደምም ሆነ ሰው ስለመገጨቱ ሊጠቁም የሚችል ፍንጭ አላገኘሁም፣ ተከሳሹን እኔ ባላነጋግረውም ከትራፊክ ፖሊስ የተነገረኝ ”አልገኝም” ብሏል የሚል ነው … ሌላ ግዜ ከአደጋ በኋላ እንዲህ ቆይቶ ምርመራ የሚደረግለት መኪና አላጋጠመኝም” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

 

የአቶ ምትኩ ግርማ (የቴዲ ጓደኛ) ምስክርነት

አቶ ምትኩ ግርማ የተባለው ሌላው ምስክር፤ አርቲስት ቴዲ አፍሮ አዲስ አበባ ጥቅምት 23 ቀን ሲገባ ከአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደተቀበለውና ሚኪስ ፋሽን የተባለ ሱቅ ሄደው ልብስ መግዛቱን፣ ፀጉሩን መስተካከሉን፣ ከዛም ምሳ በልተው ኦሎምፒያ አካባቢ ቴዲ ያሲን ወደ ተባለ ጓደኛው ጋር ሲሄድ መለያታቸውን፣ በማግስቱ ጠዋት ሲነሳ ወደ 10 የሚሆኑ የቴዲን ስልኮች ማየቱንና መልሶ ሲደውልለት ማታ ሲ.ኤም.ሲ. አካባቢ መጋጨቱንና መኪናው መንገድ ስለዘጋ እንዲያስጎትትለት ሲነግረው ጎታች ፈልጎ መላኩን፣ በኋላም መኪናው ታርጋ የለውም ተብሎ ትራፊክ ጽ/ቤት መታሰሩን፣ አስጎታቹ እንደ ደወለለት ወደ ትራፊክ ጽ/ቤት ሄዶ ታርጋው ዳሽ ቦርዱ ላይ መኖሩን እንዳሳያቸው ”መኪናው የማነው?” ብለው ሲጠይቁት ቴዲ ታዋቂ ሰው ስለሆነ በወቅቱ መናገር አለመፈለጉን፤ ነገር ግን ሲታወቅ ቤቱን አሳየን ማለታቸውንና ከቤቱ ፖሊሶች ሄደው ማሰራቸውን በመግለጽ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

 

የአቶ ያሲን (የቴዲ ጓደኛ) ምስክርነት

አቶ ያሲን የተባለ ጓደኛው ጥቅምት 23 ቀን በግምት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ እስከ ለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ፣ አቶ ሣምሶን የተባለ ጓደኛው ደግሞ በግምት ከለሊቱ አምስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አብረውት እንደነበሩና ከዚያ በኋላ እንደተለያዩ መስክረዋል።

 

ስምንተኛው ምስክር ኩባዊ ዜግነት ያላቸው ላስቬርቶ የተባሉ የምኒልክ ሆስፒታል የአስከሬም መርማሪ ሐኪም፤ አስተርጓሚ ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ በመገኘቱ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

 

ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ በሰጠው ትዕዛዝ፤ ከኩባ ተማሪዎች ማኅበር አንድ አስተርጓሚ እንዲመጣና የኩባ ኢምባሲ በትብብር አስተርጓሚ እንዲልክ ትዕዛዝ ሰጥቶ፤ መጥሪያ ደርሷቸው ያልመጡት ኮ/ል ታምራት፣ ኮ/ል ከበደ እና ሳጅን ጌትነት የተባሉ ሦስቱ የመከላከያ ምስክሮች ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

 

የሰነድ ማስረጃውን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በሬጅስትራር በኩል ከቀጠሮ በፊት ወስዶ በደረሰው ማስረጃ ላይ መልስ እንዲሰጥበት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በመስጠት ለኀሙስ ጥቅምት 6 ቀን 1999 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

በሚቀጥለው ቀጠሮ ማስረጃው ቀርቦ ከተጠናቀቀ፤ በቀጣይ በሚሰጥ አንድ ቀጠሮ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግና ተከሳሽ ቴዲ አፍሮ በሚያደርጉት ”የክርክር ማቆሚያ” ንግግር ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ በነፃ ሊያሰናብተው አሊያም ሊፈርድበት ይችላል።

 

ኀሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ጠዋት ከካናዳ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. በሲ.ኤም.ሲ. ይኖርበት ከነበረው መኖሪያ ቤቱ ”ሰው ገጭተህ አምልጠሃል” በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍርድ ቤት የሰባት ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆበት መታሰሩ ይታወሳል።

 

ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 1999 ዓ.ም. ከታሰረበት ጣቢያ የ50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ቢለቀቀም፤ በቀጠሮው መሠረትም ፍርድ ቤት ሲቀርብ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ያስተላለፈ በመሆኑ የቀጠሮ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ መዝገቡ ተዘግቷል።

 

ጉዳዩን የያዘው ፖሊስም ኅዳር 7 ቀን 1999 ዓ.ም. በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 2749/99 ቁጥር 8206/ወ/መ18 በተጻፈ መሸኛ ደብዳቤ ”ቴዎድሮስ ካሣሁን ገርማሞ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ከአስር ደቂቃ ሲሆን፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 17 ክልል በቤተ መንግሥት አካባቢ ንብረትነቱ የግላቸው በሆነው ኮድ 2-59868 አዲስ አበባ BMW አውቶሞቢል መኪናቸው ደጉ ይበልጣል የተባለ እግረኛ ገጭተው ገድለው ካመለጡ በኋላ በፍለጋ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ከዚህ ሸኚ ደብዳቤ ጋር ተልኳል።” የሚል ደብዳቤ ጽፎና ምርመራውን ማጠናቀቁን ገልጾ መዝገቡን ለአዲስ አበባ ፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስተላለፈ።

 

የቴዲ አፍሮ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ከተዘጋ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በኋላ ክስ ተመስርቶበት ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ቀረበ። የዋስ መብቱን ተከልክሎ ቃሊቲ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት ከታሰረ በሚቀጥለው ቀጠሮ ሲቀርብ ስድስት ወራት ከሦስት ቀናትን ያስቆጥራል። 183 ቀናት ይሆነዋል።

 

 

ተያያዥ

Make a Free Website with Yola.