Some things about Tedy Afro

የቴዲ አፍሮ ቃለምልልስ ከጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ጋር

Written on Saturday, August 15th, 2009 at 6:35 am by ethioforum


Tsion and Teddy15 August 2009 [Read in PDF] — ታዋቂው ድምፃዊ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ቃሊቲ በሚገኘው አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በነበረበት አንድ ዓመት ከአራት ወራት የእስር ቆይታው ቅዳሜ እና እሁድ ለሚገቡት ጠያቂዎቹ ያሳየው ከነበረው ፈገግታ አልቀነሰም። ግራና ቀኝ በአንድ ሜትር ርቀት ከተተከሉት ወገብ ላይ በሚደርሱት እንጨቶች ቆርቆሮ በተከደነው የእስረኛና የጠያቂ ግድብ ወዲያ ማዶ ቆሞ በርካታ ጠያቂዎቹን “ተጫወቱ፣ ለስላሳና ውሃ ጠጡ” እያለ ለጨዋታውም ለመጠጡም እየጋበዘ ጠያቂዎቹን በፈገግታ በጠባቂ ገደብ ከሚያጫውትበት የቃሊቲ እስር ቤት ወጥቶ፤ ያለምንም ከልካይ በእናቱ መኖሪያ ቤት በነፃነት እየተንጎራደደም ግብዣውና ጨዋታውን አላቋረጠም። ሐሙስ ዕለት በጠያቂዎቹ ብዛት ባይሳካልኝም ትላንትና አርብ ጠዋት ቃለምልልሱን በማደርግበት ክፍል አድናቂዎቹ እየገቡ ከአራት ጊዜ በላይ ቃለምልልሱን እያቆራረጥኩ ከአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ጋር አጭር ቆይታ አድርጌአለሁ። እንድታነቡት እነሆ እጋብዛለሁ።

እንኳን ለቤትህ አበቃህ!

እንኳን በሠላም አገናኘን!

የእስር ቆይታህ እንዴት ነበር?

ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። እስር ቤት፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል የመጡ እስረኞች የሚገኙበት ቦታ እንደመሆኑ፣ በተለያየ የዕድሜ የሥራ እና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች በታሰርኩበት ዞን ውስጥ ነበሩ። ከሁሉም ጋር እንደየ አስተሳሰባቸውና እንደየ ዕድሜያቸው መጠን፣ የጋራ ቤታችንም እንደ መሆኑ በጥሩ ፍቅርና መተሳሰብ አሳልፈናል።

እስሩን እንዴት አሳለፍክ?

ብዙ በማንበብ ነው ጊዜዬን ያሳለፍኩት። ምክንያቱም ቀደም ባለው ጊዜ አብዛኛው ጊዜዬን በተለያዩ ሀገሮች ለሥራ በመዘዋወር አሊያም ስቱዲዮ ውስጥ ረጅም ጊዜዬን በሥራ ስላሳለፍኩት እንደበፊቱ የማንበብ ፍላጎቴን ጠብቄ ለመቀጠል አስቸግሮኝ ስለነበር፤ አጋጣሚው መጽሕፍቶች እንዳነብ ረድቶኛልና ብዙውን ጊዜ በማንበብ ነው ያሳለፍኩት። የተወሰኑ ነገሮችንም እጽፍ ነበር። በአጠቃላይ ጥሩ ጊዜ ነው።

በሙዚቃ ሥራህ ከፍተኛ እውቅና አግኝተሃል። የበለጠ ለመሥራት በምትሯሯጥበት ጊዜ ድንገት ወደ እስር ቤት የገባህበትን የመጀመሪያ ሣምንታት እንዴት አሳለፍክ?

ለበጎም ለመጥፎም ነገር መደናገጥ ጥሩ አይደለም። ምክንያቱም ሕይወት የራሱ አካሄድና ዙር አለው። እምነት ካለ ደግሞ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የሚያደርግበት የራሱ መንገድና ምክንያት አለው። ስለዚህ ከኔ ይጠበቅ የነበረው ሁሉም መልካም እንዲሆን፣ በመልካም መንፈሥ መቆየት ብቻ ነው። በባህሪዬም ከጊዜ በኋላ እያዳበርኩት የመጣሁት ነገር፤ አስቸጋሪ ነገሮችም ሆነ በጣም አስደሳች ነገሮች ሲመጡ ስሜትን ቆንጠጥ አድርጎ ነገሮችን በሰከነ መንፈሥ ማለፍን ነው የምሞክረው። ምንም እንኳን ፍፁም ያልተጠበቀ ነገር ቢሆንም እግዚአብሔር በፈቀደው ጊዜና ሰዓት ሁሉም ነገር ስለሚሆን፤ ይቺ ቀን ደርሳ ነፃነቴን እስካገኝ ድረስ፤ በትዕግስት ጠብቄያለሁ። ምክንያቱም እኔ መነጫነጭን በሕይወቴ ውስጥ የምቀበለው መንገድ ባለመሆኑ ጥሩ ማሰብና ጥሩ መናገር በሚለው መርኅ ተመርቼ እዚህ ደርሻለሁ።

አብረውህ የነበሩት እስረኞች። አቀባበላቸውና አያያዛቸው እንዴት ነበር?

በጣም በፍቅር ነበር የያዙኝ። ሁለት ዞኖች ውስጥ ነበር የታሰርኩት። መጀመሪያው ዞን ስድስት፤ ከዛ ደግሞ ዞን አምስት ነበር የገባሁት። በመካከሉ ደግሞ ለብቻዬ የታሰርኩበት ቦታ ነበር። የመጀመሪያ ጊዜ የገባሁበት ዞን ውስጥ የነበሩት ወጣቶች ነበሩ። የተሻለ ቦታ መርጠው በእንክብካቤ ነበር ያስተኙኝ፣ ልጆችም እንዳያስቸግሩኝ መመሪያ ሰጥተውልኝ ነበር። ፍፁም ባልጠበኩት ሁኔታ ተንከባከቡኝ። በሚቀጥለው ቀን ወደ ሌላ ቦታ ነበር የሄድኩት። ይህ ቦታ መጨረሻም የነበርኩበት ዞን አምስት የሚባል ነው። በአብዛኛው በዕድሜያቸው ከፍ ያሉና ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉ ሰዎች ናቸው ያሉት። በጣም ብዙ ታሪኮችን ያጫውቱኝ ነበር። አብረን በጣም ጥሩ ጊዜ እናሳልፍም ነበር። በአጠቃላይ የሕይወት ውጣ ውረድ በጣም ብዙ ነው፤ ነገር ግን ሲወጣም ሲወረድም እንደ ቦታውና እንደ ሁኔታው ሆኖ ማለፍ ብቻ ነው ከሰው የሚጠበቀው።

ለብቻ መታሰርስ ምን ስሜት አለው?

እሱ ትንሽ ከባዱ ጊዜ ነበር። ሦስት ወር አካባቢ ብቻ ነበር የታሰርኩት።

የሙዚቃ ሥራህን ስታቀርብ በበርካታ አድናቂዎች መታጀቡን ብትለምደውም ፍርድ ቤት በምትቀርብባቸው ጊዜያት ሁሉ እንዲሁ በርካታ አድናቂዎችህን ተመልክተሃል። በችግር ሰዓት እንዲህ ሰዎች ከጎኔ ሊቆሙ ይችላሉ ብለህ አስበህ ታውቃለህ?

ፍፁም ከምጠብቀው ውጪ ነው የሆነው። ከባድ ዕዳ ነው። ምክንያቱም ለኔ ሁሉም ሰው አብሮኝ እንደታሰረ ነበር የሚሰማኝ። አስቸጋሪ ነገሮችን ሁሉ ተጋፍጦ በትዕግስት ፍርድ ቤት በመመላስ፣ አንድ ዓመት ከአራት ወር ሙሉውን እስር ቤት ባለመቅረት አብረውኝ የቆዩ በርካታ አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ህፃናት ሁሉም በየፊናውና በየደረጃው ያሳዩኝ ፍቅር መቼም ከፍዬ የምጨርሰው አይደለም። ይህን ለመክፈል እግዚአብሔር ቅንና ታማኝ አገልጋይ እንድሆን እንዲረዳኝ እለምነዋለሁ።

ቅዳሜና እሁድ በርካታ ጠያቂ ነበረህ፤ ያን ቀን በጉጉት ወይስ በጭንቀት ትጠብቀው ነበር?

እስር ቤት ላለ ሰው ቅዳሜና እሁድ እስሩ እንደ አዲስ የሚታደስበት ቀን ነው። እንደውም ቀኖቹን ያፈጥናቸዋል። ሁሉም እስረኛ የሚወደው ቅዳሜና እሁድን ነው። ቅዳሜና እሁድ ሲመጣ ደስ ይለኝ ነበር። እንዳልኩትም ሰውም አብሮ የመታሰር ያህል ነው ሲጠይቀኝ የነበረው። ቅዳሜና እሁድ ጠዋትና ከሰዓት ሳይቀሩ የሚጠይቁኝ ልጆች ነበሩ። እነዚህን ሁሉ ከልብ ለማመስገን እወዳለሁ።

ፍርድ ቤት በቀረብክባቸው ጊዜያቶች ሁለት ውሳኔዎችን ሰምተሃል። የመጀመሪያው የስድስት ዓመት እስር ከዚያ ደግሞ ሁለት ዓመት። የመጨረሻው የውሳኔ ቀጠሮ ግን ይግባኝ የማትልበት እንደመሆኑ በዕለቱ ከተሰጠው ውሳኔ በፊት በምን አይነት ስሜት ውስጥ ነበርክ?

የኔ ንግግር ከእግዚአብሔር ጋር ነው። የምወጣበትን ቀን የሚያዘጋጀውም እግዚአብሔር ነው። የምቆይበትንም ጊዜ የሚወስነው እግዚአብሔር ነው። በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር እኔን በሚጠቅመኝ ግዜና ሁኔታ ቶሎ እንደሚያስፈታኝ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበርኩ። እምነቴ እዚህ ድረስ ነበር፤ ፈጣሪም ደግሞ የሚመኙትን አያሳፍርም። የቆየሁበትም ጊዜ ብዙ ነገር የሚታይበት ስለነበረ፤ ሁሉንም ለበጎ አድርጎ ቀይሮልኛል ብዬ አስባለሁ።

በውሳኔው ስድስት ዓመቱ ቢፀና ኖሮ ሌላ የመጽናኛ አማራጭ አስበህ ነበር?

ቴዎድሮስ ባትሆን ኖሮ ማን ትሆን ነበር? አይነት ጥያቄ ነው።

አንድ ሰው ወደ አንድ ቦታ አማራጭ ሃሳቦችን ይዞ ይኼዳል ብዬ ነው፣ እግዚአብሔር እንደዛ እንደማይጨክንብኝ እርግጠኛ ስለነበርኩ ሌላ አማራጭ ሃሳብ አልነበረኝም።

በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ታሪክ ችሎት ውስጥ እንደዛ የተጨፈረበትና እልል የተባለበት ያንተ ውሳኔ ዕለት ብቻ ነው። የአድናቂዎችህ ደስታ ምን ፈጠረብህ?

እኔም ከምንም በላይ ሰው ነበር የሚያሳዝነኝ። ደስታው የራሴም ቢሆን ከምንም በላይ የሰውን ደስታ ማየቱ እጅግ ያስደስት ነበር። ምክንያቱም ሰው እንደ ራሱ ጉዳይ አድርጎ ያን ያህል ሲጨነቅ ማየት በቦታው የሆነ ሰው ብቻ ነው ስሜቱን የሚያውቀው። ስለዚህ ሰው በጣም ያሳዝነኝ ስለነበር ደስታው ሁለት አይነት ነበር።

ከውሳኔው በኋላ የእስር ጓደኞችህ እንዴት ተቀበሉህ?

እንዳልኩት እስር ቤት ውስጥ ብዙ ዓይነት ሰዎች ነበሩ። በጣሊያን ጊዜ የነበረውን ዘመቻ በሚገባ የሚያስታውሱ ሰዎች ሳይቀሩ ነበሩ። ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ስወጣ ሁሉም በጭብጨባና በደስታ ነበር የሸኙኝ። ስመለስም በጣም በደስታና በጭብጨባ ነበር የተቀበሉኝ። ደስታቸውን በቀረርቶም ጭምር በመግለጽ የተቀበሉኝ ነበሩ።

በእስር ቆይታህ ወላጅ እናትህ አልተለየችህም። ስታያት ምን ይሰማህ ነበር?

እናት መሆን ቀላል ነገር አይደለም። ከባድ መከራ ነው። እግዚአብሔር የሷን ጤንነት ጠብቆ ለዚህ ጊዜ ስላበቃኝ አመሰግነዋለሁ። መላው ቤተሰቤን በተለይ ደግሞ እናቴን እንደ መላው ህዝብ ሁሉ አመሰግናለሁ።

እስር ቤት መቆየትህን ከዕድሜህ ጋር አያይዘህ ተፀፅተህበት ታውቃለህ?

እንደሱ ቆጭቶኝ አያውቅም። ዋናው ጤንነት ነው። የቀረውም ጊዜዬ ሰፊ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር እሱን እሠራበታለሁ።

“ድምፃዊያን ችሎታቸውን ጠብቀው ለማቆየትም ኾነ ለማሻሻል ያለ ድምፅ ማጉያና ያለ ሙዚቃ መሣሪያ በቀን አንድ ጊዜ መለማመድ አለባቸው” በማለት ባለሙያዎች ይመክራሉ። በዚህ በኩል ድምፅ ችግር ተፈጥሮበታል በሚል ሰግተህ ታውቃለህ?

እንደውም በቂ እረፍት ስላደረኩ ሳይብስበት አይቀርም።

በእስር ቤት ቆይታህ በርካታ ግጥሞችን ጽፈሃል። ምን አይነት ግጥሞችን ነው የፃፍከው?

የጻፍኳቸው የዘፈን ግጥሞች አይደሉም። ለመጽሐፍ የሚሆኑ ናቸው - እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ወደፊት ይታተማሉ።

ምን ያህል ይሆናሉ?

በጣም ብዙ ናቸው።

የዘፈን ግጥሞች አልሠራህም?

አብዛኛውን ጊዜ የዘፈን ግጥም ስሠራ፣ ከዜማ ጋር አብሬ ሥለምሠራ እዛ ደግሞ ከዜማ ጋር አብሬ ለመሥራት መቅጃ መሣሪያው ስለሌለ አስቸጋሪ ነው። ብሠራም ስለሚጠፋኝ ድካም ነው የሚሆነው በሚል ብዙም አልሠራሁም። እኔም ደግሞ ከዘፈን ውጪ የሆኑ ግጥሞችን አቁሜ ስለነበረ፣ ያንን ለመጻፍ ጥሩ አጋጣሚ ሆነልኝ፤ ብዙ ብዙ ግጥም ለመጻፍ ቻልኩ።

ግጥሞችህ ነቃ ነቃ ያሉ ናቸው ወይስ ጭለማ ያጠላባቸው?

አንድ የጥበብ ሰው አፍንጫው ስር ያለውን ብቻ አይደለም ማየት ያለበት። ሁልጊዜ አሻግሮ ማየት አለበት። ብርሃን አይቶ ብርሃን ነው ማሳየት ያለበት። ሰውም አሻግሮ እንዲመለከት ምክንያት መሆን አለበት። በተነሳና በወደቀው ስር ብቻ መገደብ የለበትም። ስለዚህ ምንም ጭለማ የለም፤ ሁሉም ነገር ብርሃን ነው። ልክ እንደ “ላምባዲና” …

የማትረሳቸው አስረኞች አሉ?

ብዙ አይነት ሰዎች አሉ። አንድ ግን አባ ተካ የሚባሉ በጣሊያን ግዜ የነበሩ ሰው አሉ። እሳቸውን ምንግዜም አልረሳቸውም።

ምናቸውን ነው የማትረሳው?

በማንኛውም ሰዓት ተነስተው ቀረርቶ ያሰማሉ፤

“ጣሊያን ምን አባቱ
ቢሰፋ ደረቱ
ቢደነድን ባቱ
እንመልሰዋለን በገዛ ጥይቱ።” በማለት ቀረርቶ ያሰማሉ። የራሳቸው ብዙ የሚስቡ ባህሪ ስለነበራቸው ደስ ይሉኝ ነበር።

ሰዎች ከእስር ቤት ሲወጡ ኃይማኖታቸውን ይቀይራሉ ይባላል፤ አንተ እንዴት ነህ?

እሱ እንደ የሰዉ አይነት ይለያያል። በሰው ስሜት መግባትም አይቻልም። ነገር ግን እኔ በግሌ ቀደም ሲልም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታይ ነኝ። አሁንም በዛ እምነት ውስጥ ነው ያለሁት። ሰው የአስተሳሰብ ለውጥ ነው የሚያስፈልገው ብዬ አምናለሁ እንጂ፤ በዛ አይነት መንገድ አላምንም። ነገር ግን የሰውን ስሜት አከብራለሁ።

“የሙዚቃ ገበያ ለመዳከሙ ምክንያቱ የቴዲ መታሰር ነው” የሚሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ይህን ለመቀየር እስር ቤትም ኾነህ አሁን ለመሥራት ያስብከው ሥራ አለ?

እውነቱን ለመናገር አሁን ሰፋ ያለ የእረፍት ጊዜ መውሰድ እፈልጋለሁ። ከዛ በተረፈ የሙዚቃውን ገበያ ቴዲ ወጥቶ ያነቃቃዋል እስከሚለው ድረስ ራሴን ክቤ ለመናገር አልቀብጥም።

እስር ቤት ምን መመገብ ያስደስትህ ነበር?

ከታሰርኩበት ጊዜ እስክፈታ ድረስ በየቀኑ ከቤተሰቦቼ ምግብ ይመጣልኝ ነበር። ነገር ግን የእስር ቤቱ ሽሮ ትኩስ ሆኖ ሲመጣ ስለሚያምረኝ የራሴን ምግብ ለሰው ሰጥቼ እሱን እበላ ነበር።

እንቅልፍስ ትተኛ ነበር?

ምንም የእንቅልፍ ችግር አልነበረብኝም። አብዛኛውን ጊዜ በእንቅልፍ ነበር የማሳልፈው።

ክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ እስር ቤት ሆነህ ነው ሕይወቱ ያለፈው። ዜናውን ስትሰማ ምን ተሰማህ?

ዜናው ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ነበር የሆነብኝ። ኀዘኔን በማልቀስ ነበር የገለጽኩት። ጋሽ ጥላሁን በሕይወት እያለ እስር ቤት በነበርኩት ጊዜ ከቤተሰብ ጋር ይገናኝ ነበር። ስልክም እቤት እየደወለ ስለኔ ያለቅስ እንደነበር መልዕክት ይደርሰኝ ነበር። አንድ ጊዜ ባየው ደስ ይለኝ ነበር። እግዚአብሔር አልፈቀደም። ነገር ግን በአቀባበሩ ሥነሥርዓት ኀዘኑን ከማስረሳቱ በላይ ኩራት ተሰምቶኛል። መላውን አርቲስት ያኮራ የቀብር ሥነስርዓት ነበር። ህዝቡም የሚገባውን አክብሮት ስለሰጠው በጣም ማመስገን እወዳለሁ። ወደ መጨረሻ ሕይወቱ ላይ በጣም መቀራረብ ጀምረን ነበረ። ብዙም እንገናኝ ነበር። ከእስር ስለቀቅ አጣኋቸው ብዬ ከማስበው ሰው አንዱ ነው። እግዚአብሔር ነፍሱን በገነት ያኑረው። በበለጠ ደግሞ በሱ ጉዳይ ላይ እንጫወታለን።

  • Make a Free Website with Yola.