All about Tedy Afro

 

ቴዲ አፍሮ የስድስት ዓመት እስራት ተፈረደበት PDF Print E-mail
Friday, 05 December 2008 13:48

Teddy Afroዝርዝር ዘገባ የታከለበት

(የፍርድ ውሳኔውን ሙሉ ቃል ይዘናል)

በተጨማሪም የ18 ሺህ ብር ቅጣት ተፈረደበት

“በይግባኝ ወይንም ‘በሽምግልና’ ሊፈታ ይችላል” ታዛቢዎች

Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 26 ቀን 2001 ዓ.ም. December 05, 2008)፦ ዝነኛው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ዛሬ በዋለው ችሎት ስድስት ዓመት እስራትና 18 ሺህ ብር ቅጣት ተፈረደበት።

 

ዝርዝር ዘገባ

የዓርብ ኅዳር 26 ቀን 2001 ዓ.ም. የቴዲ አፍሮ ችሎት ውሎ

ዕለቱ ዓርብ በመሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ መውጫ ሰዓት ከቀኑ 5 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ነበር። የፍርድ ቤቱ መግቢያ በር ሳይዘጋ ወደ ግቢው በመግባት በየጥጋጥጉ ተደብቀው የችሎቱ ሰዓት ሲደርስ ተራ ለመያዝ ቀድመው የገቡትን በሙሉ የፌደራል ፖሊሶች ለቃቅመው ከግው አስወጧቸው። የወጣው ሰውና በየሰዓቱ የሚመጣው ችሎት ለመግባት ከሁለት ሰዓት በላይ ተሰልፎ መጠበቅ ጀመረ።

 

መግቢያ ሰዓት ሲደርስም “ፍርድ ቤት ጉዳይ ከሌላችሁ ሰዎች በስተቀር ማንም መግባት አይችልም” በመባሉ በእጁ የፍርድ ቤት መከታተያ ወረቀት ያለው ብቻ እንዲገባ ተደረገ። በግቢው ውስጥ ከተገባም በኋላ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ፍተሻው ተጠናክሮ ቀጠለ። ቀደም ሲል የነበረው “ሞባይላችሁን አጥፉ” ትዕዛዝ፤ “ሞባይል ይዛችሁ መግባት አትችሉም” በሚል ተቀየረ። በስንት መከራ ገብቶ የተሰለፈ ሁሉ ሞባይል ማስቀመጫ ፍለጋ መራወጥ ጀመረ። ቦታ ያገኘ አስቀመጠ፤ ያጣ ደግሞ እንዳይጋባ ተከለከለ።

 

ከቀኑ ስምንት ሰዓት የተሰየመው ችሎት ውስጥ ገብቶ እርስ በርሱ ሲነጋገር የነበረውን ችሎት ተከታታይ ሁሉ ዝም አሰኘው። ዳኛው የመዝገብ ቁጥሩንና ስማቸውን ከተናገሩ በኋላ፤ ዓቃቤ ሕግ፣ ተከሳሽና የተከሳሽ ጠበቆች መቅረባቸውን አረጋግጠው መዝገቡ የተቀጠረው ጥፋተኛ በተባለው ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት እንደሆነ ገለጹ። ከዛ በፊት ግን ለቴዎድሮስ ካሳሁን የምናገረው አለ አሉ።

 

“… ችሎቱ ይሰየምበት ከነበረው ጠባ ክፍል እዚህ ትልቅ አዳራሽ ያመጣነው፣ የመገናኛ ብዙኀን አባላትም እንዲዘግቡ ያደረግነውና ሰውም እንዲከታተለው የፈቀድነው ላንተ ክብር ስንል አይደለም፤ ፍርድ ቤትም የተቋቋመው ፍትህ ለመስጠት እንጂ አንተ እንድትደንስበት አይደለም፤ ፍርድ ቤት አንተ የምትፈልገውን እንዲባልልህ ፈልግ ከሆነ፣ ያን ልናደርግ አንችልም። ፍርድ ቤት ፍትህ መስጫ ቦታ ነው። ጉዳይህ ተራ የወንጀል ጉዳይ ነው፣ አንድ ግለሰብ ሕይወቱን ያጣበት ተራ የወንጀል ጉዳይ ይህ ቦታ የሕግ የበላይነትን አምነው የመጡ ሰዎች በእኩል የሚዳኙበት ቦታ ነው። ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ጥፋተኛ ሲልህ ፍርድ ቤቱን የምትረብሽበት፣ የምታንጓጥጥበት ምንም ምክንያት አይኖርም። …” በማለት ፍርድ ቤቱ በሰኞው (ኅዳር 22 ቀን 2001 ዓ.ም.) ችሎቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የቅጣት አስተያየት እንዳለው ሲጠየቅ “በሐቅ ለማይሠራ ፍርድ ቤት የማቀርበው የቅጣት አስተያየት የለም …” በሚል ለመለሰው መልስ የቀረበበት ወቀሳ ነበር።

 

“መናገር እችላለሁ?” ሲል ጠየቀ “አትችልም! እንኳን አንተ …” አሉና ወደ ጎናቸው ዞረው የተደረደሩትን ፖሊሶች እያዩ “እሱን ብቻ አይደለም እንደባለፈው አንድ ሲረብሽ የተገኘ ሰው በችሎት ቢኖር ከዚህ መዝገብ በኋላ በችሎት መድፈር የምናየው ጉዳይ ነው …” ሲሉ አስፈራሩ።

 

ቀጠሉና የቅጣት ውሳኔውን ማንበብ ጀመሩ። ተከሳሽ ጥፋተኛ የተባለባቸው የሕግ አንቀጾች አንደኛው፤ ከ5 እስከ 15 ዓመት ሊደርስ የሚችል እሥራት እና ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር የሚደርስ መቀጮ፤ ሁለተኛው ደግሞ ከ1 ወር እስከ 2 ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራትና መቀጮ ነው። ተከሳሹ የቅጣት ማቅለያ ሃሳብ አላቀረበም፣ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ የተፈጸመው ጥፋት ተደራራቢ በመሆኑ ቅጣቱ ከብዶ እንዲወሰንበት ጠይቋል።

 

“ፍርድ ቤቱ ወንጀሉን ሲመለከተው ተከሳሽ መኪና ለመንዳት የሚያስችል መንጃ ፈቃድ ሳይኖረው በቸልተኝነት መኪና በማሽከርከር ሰው ከገጨ በኋላ መርዳት ሲገባው ጥሎ መሄዱ ጨካኝነቱንና ነውረኛነቱን የሚያሳይ ተግባር ነው። ይህም ሊወሰን የሚገባውን ቅጣት ከባድ ያደርገዋል። ነገር ግን በተከሳሽ ላይ በቅጣት ማቅለያነት የቀረበ ሌላ የወንጀል ድርጊት ባለመኖሩ እና እሱንና ሌሎች ሰዎችን ሊያስተምር የሚችል ቅጣት ቀሎ ቢወሰን ያስተምራል ያልነውን ወስነናል።

 

“ስለዚህም በቀረበበትና ጥፋተኛ በተባለበት አንደኛው ክስ፤ የ1997 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543 (3) የሚደነግግገው “ጥፋተኛው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የገደለ ወይም ወንጀሉን የፈጸመው ግልጽ የሆነ ደንብ ወይም መመሪያ ተላልፎ እንደሆነ ወይም የሚያሰክሩ ወይም የሚያፈዙ ንጥረ ነገሮችን ወይም መጠጦችን በመውሰድ እራሱን ከኃላፊነት ነፃ በሚያወጣ ሁኔታ ውስጥ ካስገባ በኋላ ቢሆንም እንኳ፣ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራትና ከብር አሥር ሺህ እስከ አሥራ አምስት ሺህ የሚደርስ መቀጮ ይሆናል” የሚል ቢሆንም በዚህ አንቀጽ የተዘረዘረው ቀላሉ ተወስዶለት፤ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 13ሺህ ይቀጣ።

 

“በተጨማሪም በቀረበበትና ጥፋተኛ በተባለበት ሁለተኛው የ1997 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 575 (2) የሚደነግገው ደግሞ፤ “ጥፋተኛው በማናቸውም ሁኔታ ወይም ዘዴ ይሁን በተጎጂው ላይ ጉዳት ያደረሰው እራሱ ተከሳሹ እንደሆነ ወይም ተጎጂውን ለመታደግ ወይም ለመርዳት የሙያ ወይም የውል፣ የሕክምና፣ የባህል ወይም ሌላ ሕጋዊ ግዴታ ያለበት እንደሆነ፤ ከአንድ ወር እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ ቀላል እሥራት እና በገንዘብ መቀጮ ይቀጣል” የሚል ቢሆንም በዚህ አንቀጽ የተዘረዘረው ቀላሉ ተወስዶለት በአንድ ዓመት እስራትና አምስት ሺህ ብር፤ በድምሩ ስድስት ዓመት ጽኑ እስራትና 18 ሺህ ብር የገናዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል” ሲሉ ውሳኔ አስተላፉ።

 

አውልቆት የነበረው ኮት ካስቀመጠበት አንስቶ እየለበሰ “እግዚያብሔር ያውቃል” በሚል ስሜት ጣቱን ወደ ሰማይ ቀስሮ አንጋጦ ተመለከተ እናም በፖሊስ ታጅቦ ሲወጣ በሩ አካባቢ ለተሰበሰቡት የውጭ ጋዜጠኞች “I feel free” ሲል ተናገረ።

 

የቴዲ ጠበቆች የቅጣት ውሳኔው በእጃቸው ሲገባ የይግባኝ ማመልከቻ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ የታወቀ ሲሆን፤ በሦስት ዳኞች የሚሰየመው የጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ሰሚ ችሎት (በተለመደው አሠራር) የይግባኝ ማመልከቻው፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግበት ከነበረው ሙሉ መዝገብ ጋር ከደረሰው በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ በይግባኝ ማመልቻው ላይ መልስ እንዲሰጥበት አድርጎ፤ መዝገቡን በመመርመር ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ባሉ ጊዜያት ውስጥ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል።

 

የቴዲ አፍሮን ጉዳይ እየተከታተሉ የቆዩ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ ቴዲ አፍሮ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ከተቀበለውና ከክሱ በነፃ ካሰናበተው ከእስር ሊለቀቅ እንደሚችል ያላቸውን ግምት ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጠዋል። አክለውም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የፌደራሉን ፍርድ ቤት ውሳኔ ካፀደቀው፤ “ምናልባት ‘ይቅርታ’ ጠይቆ ‘በሽምግልና’ ሊፈታ ይችል ይሆናል” ሲሉ ገምተዋል።

 

የሰኞ ኅዳር 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ችሎት ውሎ

 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፤ ኅዳር 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ፤ “ፍትህ” ተብሎ በሚጠራው ሰፋ ያለ አዳራሽ፤ በአዲስ አበባና በፌደራል ፖሊስ ሥነሥርዓት አስከባሪነት፣ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ወደ አዳራሹ መግባት ተጀመረ። ዕድል ቀንቷቸውና ተራ ደርሷቸው የገቡ የተወሰኑ ወጣቶች፣ አዳራሹ በመሙላቱ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ፤ ቴዲ አፍሮን ጨምሮ ሁሉም ዓይኑን ወደ ዳኛው መምጫ ተክሎ መሰየማቸውን ይጠባበቅ ነበር። ዳኛው ከቀኑ 8፡35 ሲል ተሰየሙ።

 

መዝገቡ የተቀጠረው ለውሳኔ መሆኑን ገልጸው፤ ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ፤ ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከጠበቃቸው አቶ ሚሊዮን አሰፋና ከአቶ አመሃ በድሉ ጋር መቅረባቸውን አረጋግጠው፤ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ግራ ቀኙን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ነው ካሉ በኋላ፣ “ውሳኔ” ብለው በንባብ ማሰማት ጀመሩ።

 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፤ ኅዳር 22 ቀን 2001 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት በዳኛ ልዑል ገብረማርያም ተሰይሞ በአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ላይ “ጥፋተኛ” የተባለበትን የውሳኔ ዝርዝር ከዚህ በታች ይገኛል።

 

“ውሳኔ”

 

ዓቃቤ ሕግ በቁጥር 58243/1217/99 ሚያዝያ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በተፃፈ የክስ ማመልከቻ ላይ የመሠረታቸው ክሶች፤ አንደኛ ክስ፦ 1ኛ የ1996 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543(3) እና የትራንስፖርት ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 279/1956 አንቀጽ 5/4/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፣ ተከሳሽ ተሽከርካሪ ለማሽከርከር የሚያስችል መንጃ ፈቃድ ሊኖረው እንደሚገባ የሚዘረዝረውን ግልጽ የሆነ ደንብ በመተላለፍ፣ መንጃ ፈቃድ ሳይኖረው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ሲሆን፣ የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2- 59869 አዲስ አበባ የሆነ ቢ.ኤም.ደብሊው. አውቶሞቢሉን እያሽከረከረ ሲጓዝ፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 17 ልዩ ቦታው ፊት በር በተባለ አካባቢ ሲደርስ፣ መንገዱን ከቀኝ ወደ ግራ በማቋረጥ ላይ የነበረውን ሟች ደጉ ይበልጣል የተባለውን ቅድሚያ በመከልከል ገጭቶ በመግደሉ፣ በፈፀመው በቸልተኝነት ሰው መግደል ወንጀል ተከሷል።

 

ሁለተኛ ክስ፦ በ1996 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌደራል የወንጀል ሕግ አንቀጽ 575 (2) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሽ ከላይ በ1ኛው ክስ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ፣ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 2-59869 አዲስ አበባ የሆነ ቢ.ኤም ደብሊው አውቶሞቢሉን እያሽከረከረ ሲጓዝ፣ ሟች ደጉ ይበልጣል ይባል የነበረውን ከገጨ በኋላ፣ ተገጪው ሕይወቱ በከባድ አደጋ ላይ መሆኑን እያወቀ ዕርዳታ ሳያደርግለት ጥሎት በመሸሽ በፈፀመው በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰው አለመርዳት ወንጀል ተከሷል የሚሉ ናቸው።

 

ተከሳሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ፣ የክሱ ማመልከቻ ደርሶትና እንዲረዳውም ተደርጎ፣ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ፣ ክዶ በመከራከሩ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮችና የሠነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል።

 

በዓቃቤ ሕግ የቀረቡ ምስክሮች፣ አደጋው ሲፈፀም ፀጥታ በማስከር ሥራ ላይ ተሠማርተው የነበሩ ፖሊሶች፣ የአደጋውን ፕላን ያነሳ ትራፊክ ፖሊስ፣ እንዲሁም በፍ/ቤቱ በማጣሪያ ምስክርነት የተጠራው የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከተሰጠበት ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተላከ ባለሞያ እና በሠነድ ማስረጃ ረገድ ደግሞ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ለፖሊስ የሰጠው የምስክርነት ቃል፣ የአስከሬን የምርመራ ውጤት፣ አደጋውን የሚያመለክት ፕላን፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ውጤትና የሟችን ገፅታ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ናቸው።

 

ምስክሮቹም በክሱ ማመመልከቻው ላይ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ በፀጥታ ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ገልፀው ተከሳሽ የሚያሽከረክረው መኪና የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2-59869 አ.አ. ሟች ደጉ ይበልጣልን በመግጨት ሸሽቶ ሲያመልጥ ሟችም ወዲያውኑ ሕይወቱ ሲያልፍ በማየታቸው ስለሁኔታው ለትራፊክ ፖሊስ አስቀርበው ባለሙያ ተልኮ ሟች ባለበት ሁኔታ የአደጋውን ቦታ ፕላን መነሳቱንና ሟች የአስክሬኑ ምርመራ ወደሚደረግበት የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል መወሰዱንና አንደኛው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ከሦስተኛው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ጋር በመሆን አደጋውን መመልከቱን በዕለቱም የተሽከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር መመዝገቡን በተለይም ትራፊክ ፖሊሱ እንደመሰከረው፤ ተከሳሹና አደጋውን ያደረሰው የተከሳሸ ተሽከርካሪ አደጋው በደረሰበት ማግሥት ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መያዛቸውን እና ተከሳሹ በወቅቱ የመንጃ ፍቃድ እንዳልነበረው ጭምር አስረድቷል።

 

የአስከሬን ምርመራው ከተደረገበት፣ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተላከ የሕክምና ባለሞያ በበኩሉ፤ የአስከሬን ምርመራ ውጤቱን የሚያስረዳው የሕክምና ማስረጃ የተፃፈበት ቀን፣ ክርክር በማስነሳቱ እንዲያስረዳ ተጠይቆ፣ የቀኑ ስህተት የተከሰተው የአስክሬን ምርመራውን ባደረጉት ሐኪም የአፃፃፍ ግድፈት፣ አስከሬኑ ወደ ሆስፒታሉ የገባበት ቀን በክሱ ላይ እንደተመለከተው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን፣ የአስከሬኑ ምርመራው የተደረገበት ቀን ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. እንደሆነ አስከሬኑ ለምርመራ ሲገባ ከምርመራው ቅፅ ወይም ፓድና ምርመራው ሲደረግ ውጤቱ ከሚመዘገብበት ሠነድ መገንዘቡን በችሎት አስረድቷል።

 

በሠነድ ማስረጃ ረገድ ሁለተኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ለፖሊስ የሰጠው የምስክርነት ቃል፣ ሟች ለሞት የበቃው በደረሰበት አደጋ ምክንያት መሆኑን የሚያመለክተው ፕላንና፣ የተሽከርካሪው የቴክኒክ ምርመራ ውጤትና የሟችን ውጫዊ አካላዊ ጉዳት የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ቀርበው ፍርድ ቤቱ ተመልክቷቸዋል። ዝርዝር ሐተታው ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በሰጠው ብይን መሠረት መስከረም 29 ቀን እና ጥቅምት 6 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋሉት ችሎቶች፣ ጽ/ቤቱ መከራከሪያውንና የተከሳሹን ቃል የመከላከያ ምስክሮች የምስክርነት ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን ይዘት እንደሚከተለው እንመልከታቸው።

 

ዶ/ር ይርዳው አሻጋሪ፦ የተባሉት የተከሳሽ የመከላከያ ምስክር ኅዳር 4 ቀን 1999 ዓ.ም. በተሰጠው የሟች ደጉ ይበልጣል የአስከሬን ምርመራ የምስክር ወረቀት ላይ መፈረማቸውን ገልጸው የፈረሙበት ምክንያትም የአስክሬን ምርመራው ውጤቱን የሥራው ባለሞያ ፊርማ በማየት መሆኑን አስረድተው፤ “በመዝገቡ ላይ የሠፈረ ነገር ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መቀየር ይቻላል ወይ?” ለሚለው የተከሳሽ ጠበቃ ጥያቄ፤ በፍርድ ቤትም ኾነ በሌላ ሕጋዊ አካል ጥያቄ ሲቀርብ የአስከሬን ምርመራ ውጤቱን ዋና ይዘት ሳይሆን፣ የቀን ስህተት ወይም ግድፈት እንደሚያጋጥም ሊስተካከል እንደሚችል ስለ አሠራሩም የአስከሬን ምርመራ የተደረገለት ሟች ማንነት ተጠቅሶ ከፖሊስ ጥያቄ ሲቀርብ፣ የአስከሬን ምርመራውን የሚመለከቱ ሠነዶች በዝርዝር በማየት የቀን ግድፈት መኖሩን ከታወቀ፣ ትክክለኛውን ቀን በመመልከት ከይቅርታ ጋር ሆስፒታሉ ለጠየቀው አካል ደብዳቤ እንደፃፉ አብራርቷል።

 

ዶ/ር ካሳሁን አደም፦ የተባለው ሰባተኛ የመከላከያ ምስክር፣ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዲፓርትመንት ኃላፊ ኾኖ ሲወከልም፣ የሆስፒታሉ አስተዳደር ኾኖ እንደሚሠራ ገልፆ በ13/10/2000 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለትራፊክ መቆጣጠሪያ ምርመራ መምሪያ ከሆስፒታሉ በተፃፈው የሟች ደጉ ይበልጣል የአስከሬን ምርመራ ውጤት፣ የምስክር ወረቀት ላይ መፈረሙን አስረድቶ፣ ለመፈረም ምክንያት የሆነውም ቀደም ሲል ከሆስፒታሉ የተጠቀሰው የሟች የአስክሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት የቀን ስህተት ስለነበረበት፣ በዓቃቤ ሕግና በፖሊስ ለሆስፒታሉ በቀረበ ጥያቄ መሠረት፣ የሟች አስክሬን ለምርመራ ወደ ሆስፒታል የገባበት ቀን ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከለሊቱ 7 ሰዓት ከ15 ደቂቃ መሆኑንና፣ ምርመራ የተደረገበት ቀን ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. እንደሆነ ከአስከሬን መረከቢያ ቅፅ እንዳሁም ምርመራው ሲደረግ ከተመዘገበበት መዝገብ በማየት፣ በቀን አመዘጋገብ የተከሰተውን ግድፈት በማረም የተስተካከለ የአስከሬን የምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት መስጠት ያለበት በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል።

 

ይህንንም አሠራር ስህተት ባጋጠመ ጊዜ ሁሉ የሚደረግ መሆኑን፣ ከቀን ማስተካከል በቀር በአስከሬን ምርመራ ውጤቱ ይዘት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳልተደረገ፣ በአስከሬን የምርመራ ውጤቱ ምስክር ወረቀት ላይ የሚፃፈው ቀን አስክሬኑ ወደ ሆስፒታል ሲገባ የአስከሬን ምርመራ እንዲደረግ፣ ከአስከሬኑ ጋር ሆስፒታሉ የሚረከበውን የፖሊስ የምርመራ መጠየቂያ ቅፅ እና ምርመራ የተደረገበትን ቀን፣ የተመዘገበበትን የሆስፒታሉ መዝገብ መሠረት በማድረግ እንደሆነ፣ አስከሬኑ ወደ ሆስፒታሉ የገባበት ቀን ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን የሚያስረዳው ወረቀት አሁንም በእጁ እንዳለና አስከሬኑ የተመረመረበት ቀን ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን፣ በአስከሬን ምርመራ ረዳት ሞርቲሻን አማካኝነት ተመዝግቦ እንደሚገኝ፣ ነገር ግን አስከሬኑ ምርመራ ያደረገችው ሐኪም አስከሬኑ ወደ ሆስፒታሉ ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. መግባቱንና ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ምርመራ እንደተደረገበት በመግለጽ የሰጠችው የምስክር ወረቀት የተሳሳተ መሆኑን፣ አስከሬኑ በፖሊስ ጥያቄ ወደ ሆስፒታሉ የገባው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከለሊቱ 7 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ሲሆን፣ ምርመራ የተደረገለት ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን አጣርቶ የተስተካከለውን የአስከሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት መስጠቱን ገልጾ፣ ከዚህም የምርመራ መጠየቂያ ወረቀት ሳይኖር ሆስፒታሉ አስከሬን እንደማይቀበል ጨምሮ መስክሯል።

 

አብርሃም መሰለ፦ የተባለው ስድስተኛ የመከላከያ ምስክር፣ በሆስፒታሉ የአስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ ሆኖ እንደሚሠራ፣ ከሆስፒታሉ በቁጥር በ4777/44/2000 በ13/10/2000 በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለትራፊክ መቆጣጠሪያ ምርመራ መምሪያ በተፃፈ ደብዳቤ የተፈረመ መሆኑን ገልጾ፣ ሟች ደጉ ይበልጣል ለአስከሬን ምርመራ ወደ ሆስፒታሉ የገባው ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑንና የአስከሬን ምርመራ የተደረገለት ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. እንደሆነ ገልፆ፣ ኅዳር 4 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሆስፒታሉ ለትራፊክ ፖሊስ መቆጣጠሪያና ምርመራ መምሪያው የተፃፈው መሆኑን በመግለፅ የሟች ደጉ ይበልጣል አስከሬን ወደ ሆስፒታሉ የገባበት ትክክለኛ ቀን ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን፣ የአስከሬን ምርመራ የተደረገበት ቀን ከጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን የሚገልፅ እንደሆነ አስረድቶ ስህተቱ የተፈጠረው የአስክሬን ምርመራ እንዲደረግ የሚጠይቀው የፖሊስ ፓድ፣ በአማርኛ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. የሚል ቢሆንም፣ ምርመራውን ያደረገችው ሐኪም አስከሬኑ የገባበት ቀን በስህተት በእንግሊዘኛ ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ብላ ከዋናው ሠነድ የተለየ ቀን የሰፈረበት ምስክር ወረቀት በመስጠቷ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

 

ጉዳዩ በዋናው መዝገብ ላይ መሥፈር አለመሥፈሩን ለማየት ግን፣ ሞያው ስለማይፈቅድለት የክፍሉ ባለሞያዎች በሚሰጡት መረጃ መሠረት፣ የሟች ደጉ ይበልጣል አስከሬን ለምርመራ ወደ ሆስፒታሉ የገባው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን፣ ምርመራው የተደረገለትም ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን የሚገልፅ የታረመ ደብዳቤ ለክፍሉ መፃፉን በመግለጽ መስክሯል።

 

ዶ/ር ላዲስፔርቶ ሞያአላርኮን የተባለው አራተኛ የተከሳሽ ምስክር በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ስፔሻሊስት መሆኑን፣ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሞያዊ ማብራሪያ ለመስጠት በዚሁ ፍ/ቤት ቀርቦ እንደነበረ ገልፆ፣ ከአሁን በፊት ፈርሜበታለሁ ያለውን የሟች የአስክሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት እንዲመለከተው ተደርጎ፣ በምስክር ወረቀቱ ላይ የተፃፈውን በማየት፣ ሟች ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ውጤቱን መሞቱን፣ ሟች ለሞት የበቃውም በልዩ ልዩ የአካል ክፍሎቹ ላይ ጉዳት ደርሶበት መሆኑን በሀገሩ አስራር ሐኪሞች ራሳቸው በአካል አይተው ካላረጋገጡ በቀር አንድ ሰው የሞተበትን ቀን አይተው ለመገመት እንደማይችሉ፣ የሟች ደጉ ይበልጣልን አስከሬን አለመመርመሩን ነገር ግን ከእርሱ በፊት በሆስፒታሉ የነበረችው ባለሞያ የአስከሬን ምርመራውን ማካሄዷን የአስከሬን ምርመራ ባለሞያ መሆኗን እንደሚያውቅ የማስተካከያ ምስክር ወረቀት በሆስፒታሉ ሲፃፍ የአስከሬን ምርመራውን ያደረገችው ሐኪም ባትኖርም እሷን ተክቶ ሥራውን ስለሚሠራ በዚሁ ኃላፊነቱ መፈረሙን፣ ስህተት ሲያገኝም ስህተቱን ማረም የተለመደ አሠራር መሆኑን፤ ይህም የሚደረገው ስህተቱን ለማስተካከል ከፖሊስ የመጣውን መረጃ በማየት መሆኑን፣ የአስከሬን ምርመራ ሲሰጥ ትንተና የሚደረገው፤ ሟች የሞተበትን ጊዜ፣ ሟች ለሞቱ ምክንያት የሆኑ ምልክቶች እና ከሞተ በኋላ የሚታዩ ምልክቶች መሆናቸውን፣ እነዚህ ምልክቶች ግን ፖሊስ በሚያቀርበው መረጃ የማይለወጡ መሆናቸውን በማስረዳት፣ ሟች የሞተበት ቀንና ምክንያት ከሕክምና ባለሞያው ውጪ ፖሊስ ማረጋገጥ እንደማይችል፣ የሕክምና ባለሞያውም ቢሆን አንድ ሰው የሞተበትን ቀን ለመገመት ሞያዊ ስሌት እንደሚያስፈልገው፣ ከግምት ያለፈ ትክክለኛውን ቀን ለመወሰን የሚቻለው፣ የአስከሬን ምርመራ በማድረግ መነሻ የሚሆነው ከፖሊስ የሚመጣ መረጃ መሆኑንና የአስክሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት ሲሰጥም ዋናው መረጃም ሆነ ታርሞ በቀረበው የአስክሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት ላይ ሲፈረም፣ የዶክተሯ የምርመራ ውጤት ማየቱን የሆስፒታሉን የመመዝገቢያ ሰነድ ጭምር መመልከቱንና ሟች የሞተበት ትክክለኛው ቀን ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. የአስከሬን ምርመራ መደረጉን፣ ቀደም ሲል ከፖሊስ የተፃፈው ኦርጅናል ማረጋገጫ ወረቀት ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. የተፃፈ ቢሆንም፣ ምስክሩ በወቅቱ ከኢትዮጵያ ውጭ ስለነበር አለማየቱን ምርመራው የተደረገበት ቀን ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን ግን መመልከቱንና የማስተካከያ ምስክር ወረቀቱ የተፃፈውም፣ ከፖሊስ የቀረበውን የማረጋገጫ ሠነድ መነሻ በማድረግና፣ የሆስፒታሉን ሠነዶች በመመልከት እንጂ ድጋሚ ምርመራ ያልተደረገ መሆኑን፣ የተደረገው እርማትም የቀን ስህተት ለማስተካከል እንጂ በምርመራው ውጤት ዋናው ይዘት ላይ እንዳልሆነ መስክሯል።

 

ም/ል ኢ/ር መሐመድ ገነም የተባለው ምስክር፦ የተሽከርካሪውን የቴክኒክ ምርመራ ከአንድ ሌላ የፖሊስ ባልደረባ ጋር ማድረጉን ገልፆ፣ ምርመራው ሲደረግ ተከሳሸ ለመቅረብ ፈቃደኛ ስላልነበረ አለመገኘቱን፣ መኪናው ፊት በር አካባቢ አደጋ ማድረሱ እንደተነገረው፣ ይህ መኪና በመጀመሪያ ፊት በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰው ገጭቶ ማምለጡን፣ በኋላም ከግዑዝ ነገር ጋር ተጋጭቶ መገልበጡን ከፖሊስ ሪፖርት መረዳቱን፣ መኪናው ጥቅምት 23 ቀን አደጋ ማድረሱንና፣ ኅዳር 6 ቀን ምርመራ የተደረገለት መሆኑን፣ በመጀመሪያው አደጋ ከደረሰ በኋላ ባለመቆሙ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ባለማድረጉ፣ መኪናው በሌላ ቦታም አደጋ ስለደረሰበት፣ ጉዳቱ ከመጀመሪያው ግጭት ጋር የተያያዘ ነው ብሎ መለየት አስቸጋሪ መሆኑን፣ ምርመራ የተደረገለት አደጋው ከደረሰ ከ13 ቀናት በኋላ በመሆኑም ሰው ከመግጨቱ ጋር በተያያዘ እንደ ደም የመሳሰሉትን ምልክቶች በአቧራ ሊጠፋ ስለሚችል መለየት አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ በመኪናው ላይ ስለደረሰው ጉዳት አይቶ መመዝገቡን፣ ተከሳሽ በአካል ስላልቀረበና አደጋውም ሞትን ያስከተለ በመሆኑ ተከሳሸ በሌለበትም ቢሆን እንዲመረምር ከኃላፊው በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ ጉዳዩን የሚያውቀው መርማሪ በሰጠው መረጃ መነሻነት የቴክኒክ ምርመራውን ለሁለት ሆነው ማከናወናቸውን፣ ይህ የቴክኒክ ምርመራ አደጋው ከደረሰበት ጥቅምት 23 ቀን 1999 በኋላ ኅዳር 6 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን፣ በቴክኒክ መሆኑንና እርሱም እንደፈረመበት አይቶ ማረጋገጡን መስክሯል።

 

ከበደ ወዮሳ የተባለው ዘጠነኛ ምስክር፦ እንዲነገር የተፈለገው ጭብጥ የፖሊስነት የቅጥር ዘመኑን በተመለከተ ነው። በዚሁ መሠረት ምስክሩ በ1998 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር አንስቶ የፖሊስ ባልደረባ መሆኑን፣ በዚሁ ጉዳይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ በዚሁ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር ገልፆ፣ በፖሊስ ሠራዊት የወንጀል መከላከያ አባል መሆኑንና በዚሁ ምክንያት ሁርሶ ማሠልጠኛ ለአራት ወራት ያህል መሠልጠኑን፣ አደጋው ደረሰ በተባለበት ጊዜ ከምሽቱ 1 ሰዓት አንስቶ እስከ 12 ሰዓት ተመድቦ ይሠራ እንደነበር፣ ይህ ተመድቦ ይሠራበት የነበረው ቦታም አራዳ ክ/ከተማ ቀበሌ 17 ክልል እንደሆነ፣ በወቅቱ አደጋውን ያደረሰውን መኪና ማየቱን፣ መኪናውም አረንጓዴ ቀለም የቤት መኪና መሆኑን ማየቱንና፣ መኪናው በፍጥነት ሲሽከረከር እንደነበር፣ አሽከርካሪውን ለይቶ እንዳላየውና አደጋው ከደረሰበት ቦታ ከ20 ሜትር ርቀት ላይ እንደነበር መስክሯል።

 

ምትኩ ግርማ፦ የተሰኘው አንደኛው የመከላከያ ምስክር፣ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. በግምት 2፡30 ጧት ተከሳሹን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከተቀበለው በኋላ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ አብሮት እንደቆየና፣ ኦሎምፒያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደተለያዩ፣ ተከሳሹ ያሲን ከተባለ ጓደኛው ጋር መሄዱን ገልፆ፣ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ከጧቱ 12፡30 ተከሳሽ እንደደወለለት ከስልኩ በመረዳቱ፣ ወደ ተከሳሽ መልሶ ሲደውል ሲ.ኤም.ሲ. አካባቢ ሳህሊተ ምህረት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት፣ ከአፈር ጋር ተጋጭቶ አደጋ ስለደረሰበት መኪናውን እንዲያነሳለት ተከሳሽ ጠይቆት ሄዶ መኪናውን በጐታች መኪና እንዳስነሳለት፣ መኪናው ታርጋ የለውም ተብሎ በመቆሙ ተጠርቶ ሄዶ፣ ታርጋው ከመኪናው ዳሽ ቦርድ ላይ ተገልብጦ እንደነበር በማሳየቱ፣ መኪናው ወደ ትራፊክ ጽ/ቤት መወሰዱንና መኪናው የቴዎድሮስ ካሣሁን ንብረት መሆኑን ለጽ/ቤቱ መናገሩንና፣ ከሁለት ፖሊስ ጋር ሆኖ ወደ ተከሳሽ ቤት ሄደው ተከሳሹን እንዳገኙት መስክሯል።

 

ያሲን ከድር የተባለው ምስክር፦ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰዓት፣ ከኦሎምፒያ አካባቢ ተከሳሹን እንዳገኘውና፣ ተያይዘው ወደ ምስክሩ ቤት በመሄድ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ቆይተው፣ ከዚያ ከሰዓት በኋላ ኦሎምፒያ አካባቢ በሚገኙ መዝናኛ ቤቶች እስከ ለሊቱ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ማምሸታቸውንና በየራሳቸው መኪና፣ ተከሳሽ የራሱን መኪና ይዞ መለያየታቸውን፣ ከተለያዩ በኋላ ወደ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ተከሳሽ ደውሎ አደጋ ደርሶብኛል ብሎ እንደነገረውና በማግስቱ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ጧት መኪናውን ለማስነሳት ሄዶ መኪናውን እንዳላገኘውና ሁለት ፖሊሶች በተከሳሽ ቤት እንደነበሩ ማየቱን ገልጿል።

 

ሳምሶን አቢሶ የተባለው ሦስተኛው ምስክር፦ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከምሽቱ 5 ሰዓት፣ መስቀል ፍላወር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ስሙን ለይቶ በማያውቀው መዝናኛ ቤት፣ ከተከሳሽና ከሁለተኛው የመከላከያ ምስክር ጋር ተገናኝተው፣ እስከ ለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ቆይተው፣ የየግል መኪናቸውን እያሽከረከሩ ምስክሩ ወደ ቦሌ አቅጣጫ መሄዱንና፣ ተከሳሽም መኪናውን እያሽከረከረ ወደ ባምቢስ አቅጣጫ በመሄድ፣ ደንበል መብራት አካባቢ መለያየታቸውን ገልፆ፣ በማግስቱ ተከሳሹ መኪና እንደተጋጨበትና ሰው ገጭቷል መባሉን እንደሰሙ መስክሯል።

 

ተከሳሽ የሰጠው ቃል፦ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ መግባቱንና፣ ከዚያም በኋላ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከአንደኛው የመከላከያ ምስክር ጋር እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ ቆይቶ፣ በዚሁ ምስክር እጅ የቆየችውን መኪናውን ተቀብሎ ከሁለተኛው ምስክር ጋር በመሆን ወደ ሁለተኛው ምስክር ቤት አብረው ሄደው፣ እስከ ምሽቱ 3፡30 ወይም 4 ሰዓት ቦሌ ወደሚገኘው አንድ መዝናኛ ቤት እንደሄዱና፣ ከሦስተኛው ምስክር ጋር በግምት እስከ ከምሽቱ 8፡30 እስከ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ አምሽተው በየግል መኪናቸው እስከ ኦሎምፒያ ድረስ በመምጣት እንደተለዩ ተከሳሹ መኪናውን ይዞ በባምቢስ አቅጣጫ መሄዱን ገልፆ፣ ወደ ቤት የመሄድ ሃሳቡን በመቀየር ለመዝናናት ማሲንቆ ተጫዋቾች ወዳሉበት መዝናኛ ቤት ሄዶ መቆየቱን፣ ከዚያም ወደ ቤቱ ለመሄድ በማሽከርከር ለይ እንዳለ ከነበረበት የእንቅልፍ መጓደል የተነሳ፣ ከግዑዝ ነገር ጋር መጋጨቱንና በሌላ ሰው ዕርዳታ (ሊፍት) ተሰጥቶት ወደ ቤቱ መግባቱንና፣ ስለ አደጋው ለመንገር ወደ አንደኛው መከላከያ ምስክር ስልክ ደውሎ፣ ወዲያውኑ ባያገኘውም በማግሥቱ ከጧቱ 12 ሰዓት ሲሆን፣ እንዳገኘውና እንደገና ከአንደኛው የመከላከያ ምስክር ጋር ተደዋውለው፣ መኪናው ተጋጭቶ መንገድ ላይ መቆሙን ገልጾ እንዲያነሳለት መጠየቁን፣ አንደኛው የተከሳሽ የመከላከያ ምስክር ተከሳሽ በጠየቀው መሠረት የተጋጨውን መኪና አስነስቶ ሲወስድ፣ ታርጋ የለውም ተብሎ መያዙን ተደውሎለት ፖሊሶች መጥተው ከቤቱ ወስደውት፣ ትራፊክ ጽ/ቤት ሄዶ ስለሁኔታው ማስረዳቱን ገልፆ ገጭተህ ገድለሃል ተብሎ የተከሰሰበት ግለሰብ እሱ በሌለበት ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. የሞተ መሆኑንና፣ እሱ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የገባው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. እንደሆነ ፍርድ ቤቱ እንዲረዳለት ጠይቋል።

 

ተከሳሸ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ሟች ደጉ ይበልጣል ሕይወቱ ያለፈበትን የአስክሬን ምርመራ የተደረገበትን ቀናት የሚያመለክቱ በቁጥር 256/44/99 ኅዳር 4 ቀን 1999 ዓ.ም. ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተፃፈ።

 

ተከሳሽ ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. በሀገር ውስጥ ያልነበረ መሆኑን የሚያመለክት የተከሳሽ ፓስፖርት፣ ቪዛና ከቦሌ ኢምግሬሽን የተሰጠ ወደ ሀገር ውስጥ መግቢያ ማረጋገጫ፣ ተከሳሽ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የሚያረጋግጥ በቁጥር 75/10/00/08/2 ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን፣ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መምሪያ፣ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ ለልደታ ምድብ የወንጀል ችሎት የፃፈውን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማመልከቻ ነው።

 

ኮንስታብል ታምራት ዱላ የተባለው ሁለተኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ጥቅምት 24 ቀን ለፖሊስ የሰጠው የምስክርነት ቃል፣ በቁጥር 4777/44/2000 በ13/10/2000 የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ መቆጣጠሪያ መምሪያ የፃፈው ሲሆን፣ ፍ/ቤቱ ተመልክቷቸዋል። ተከሳሽ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ለትራፊክ ፖሊስ የሰጠው ቃል ተያይዟል።

 

ፍርድ ቤቱ ክሶቹ የግራ ቀኝ ማስረጃዎችና ክርክሮቻቸውን ከላይ እንደተመለከተው፣ ፍ/ቤቱ የአቃቤ ሕግ ማስረጃ እንደክሱ አስረድቷል? አላስረዳም? ተከሳሽ የቀረቡበትን ክሶችና ማስረጃዎች አስተባብሏል? አላስተባበለም? የሚሉትን ጭብጦች በመያዝ መርምሮታል። ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል? አላስረዳም የሚለው በብይን ወቅት ስለተባለ አይደገምም።

 

1ኛ፣ 2ኛ፣ እና 3ኛ የመከላከያ ምስክሮች ያስረዱለታል ተብሎ የተያዘው፣ ጭብጡ ከላይ በዝርዝር እንዳሰፈረው፣ በይዘቱ ተመሳሳይነት ያው ሲሆን፣ 1ኛው የመከላከያ ምስክር ተከሳሽን ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመሄድ ተቀብሎት፣ ከዚያ እጁ ላይ የቆየችውን መኪናውን ለተከሳሽ አስረክቦት ከጓደኛው የመከላከያ ምስክር ጋር እስከተገናኙበት ሰባት ሰዓት ድረስ አብሮት እንደቆየና እንዳልተለየው መስክሮ በማግስቱ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ከጧቱ 12 ሰዓት ሲሆን፣ ማን ቀድሞ እንደደወለ ባልተለየበት ማለትም ተከሳሽ እኔ ደውዬለት ነበር ሲል፣ ምስክሩ በበኩሉ ቀሪ ጥሪ (ሚስድኮል) አግኝቼ ደወልኩለት እንጂ ተከሳሽ አልደወለልኝም በማለት እርስ በርሱ ባልተጣጣመ አነጋገር ምስክሩ እንደገለፁ፣ ተከሳሽ መኪናው ከለሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ ሲ.ኤም.ሲ. ተብሎ በሚጠራው፣ ልዩ ቦታው ሳሊተ ምህረት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት መኪናው አደጋ ደርሶበት መቆሙን ተከሳሽ ነግሮት፣ በመኪና ጐታች አስነስቶ መኪናውን በማስወሰድ ላይ እንዳለ፣ መኪናው ታርጋ የለውም በሚል በትራፊክ ፖሊስ ተይዞ ተደውሎለት ሄዶ፣ ታርጋው ዳሽ ቦርዱ ላይ ተገልብጦ በነበረበት እንዳስቆሙ፣ ከትራፊክ ጽ/ቤት ፖሊሶች ጋር በመሆን ወደ ተከሳሹ ቤት ሄደው ፖሊሶች ተከሳሽን እንደወሰዱት ገልጿል።

 

2ኛ እና 3ኛ የመከላከያ ምስክሮች በበኩላቸው፣ ተከሳሽ በተለምዶ ከ2ኛው ምስክር ጋር ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እስከ ለሊቱ 9 ሰዓት ሳይለያዩ አብረው እንደቆዩ የገለፀ ሲሆን፣ 3ኛውም የመከላከያ ምስክር ከምሽቱ 5 ሰዓት ጀምሮ እስከ ለሊቱ 9 ሰዓት ድረስ፣ በተለምዶ ከተከሳሽ ጋር ሦስት ሆነው አብረው መቆየታቸውንና ከዚህም በኋላ ተከሳሽ የግሉን መኪና እያሽከረከረ ወደ ሲ.ኤም.ሲ. አቅጣጫ መሄዱንና እነርሱም የየግል መኪናቸውን ይዘው ወደ የቤታቸው መሄዳቸውን ገልፀው፣ ተከሳሽ በተለይ ወደ 2ኛው ምስክር በመደወል መኪናው መጋጨቱን እንደነገረውና፣ እነዚሁ ምስክሮች በማግሥቱ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም.፣ ተከሳሽ ሰው ገጭቷል በሚል ክስ እንደቀረበበት መስማታቸውን በተለምዶ 2ኛው የመከላከያ ምስክር፣ ተከሳሹን ፖሊስ ይዞት ሲሄዱ ማየቱን መስክሯል። እነዚህ የመከላከያ ምስክሮች ያስረዱት ጭብጥ፣ ተከሳሽ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱንና እስከ ለሊቱ 9 ሰዓት ድረስ መስቀል ፍላወር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኙ መዝናኛ ቤቶች ሳይለያዩ አብረው ማምሻቸውን ከዚህ ሰዓት በኋላ ግን ተከሳሽን ጨምሮ የየግል መኪናቸውን ይዘው ወደየቤታቸው እንደሄዱ፣ ተከሳሽ ከዚህ ሰዓት በኋላ መኪናው ተገጨብኝ ብሎ ደውሎ ከነገራቸው በቀር ሌላ ምን አደጋ እንደገጠመው እንደማያውቁ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ተከሳሽ በሰጠው ቃል ከመከላከያ ምስክሮቹ ጋር በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ አብሮአቸው እንደቆየ፣ በግምት ከ8 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት መኪናውን ይዞ ከእነሱ ከተለየ በኋላ ብቻውን ማሲንቆ ተጫዋቾች ወደሚገኝበት “ይወደል” ተብሎ በሚጠራው መዝናኛ ቤት ቆይቶ 9 ሰዓት ተኩል አካባቢ ወደ ቤቱ ሲሄድ፣ በመከላከያ ምስክሮች እንደተነገረው የመኪና መጋጨት አደጋ እንደደረስበት ለፍ/ቤቱ ገልጸዋል።

 

እነዚህ ፍሬ ነገሮች በአንድ ላይ ሲታዩ ተከሳሽ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. በሀገር ውስጥ እንደነበርና፣ መኪናውን ከ1ኛው መከላከያ ምስክር በዚሁ ዕለት ተረክቦ ሲጠቀምበት መዋሉንና ማምሸቱን፣ ከተከሳሸ በቀር በዚሁ ተሽከርካሪ የተጠቀመን ሆነ ያሽከረከረ ሰው አለመኖሩን፣ ተከሳሽ በተለምዶ ከመከላከያ ምስክሮቹ ተለይቶ ብቻውን ሲያሽከረክር 2ኛውና 3ኛው ምስክሮች እንደተናገሩት፣ ኦሎምፒያ ወይም ደንበል መብራት አካባቢ መለያየታቸውን እንጂ ከዚያ በኋላ ስለሆነው ከተከሳሽ በቀር የሚያውቅ አለመኖሩንና 2ኛውና 3ኛው ምስክር እንደገመቱት፣ ተከሳሽ ሲ.ኤም.ሲ. አቅጣጫ ወደቤቱ ሳይሆን ብቻውን ወደ ተለያዩ መዝናኛ አካባቢዎች መሄዱንና ከዚያ በኋላ ወደ ቤቱ ሲሄድ መኪናውን ከግዑዝ ነገር ጋር መጋጨቱን ነው።

 

የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሰጡት የምስክርነት ቃል፣ ንብረትነቱ የተከሳሽ መሆኑን ያልተለየው፣ በምስክሮቹ አነጋገር አረንጓዴ ቀለም የቤት መኪና የሠሌዳ ቁጥር 2-59869 አ.አ. የሆነ፣ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ከለሊቱ 7 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በፍጥነት ሲያሸከረክር፣ ደጉ ይበልጣል የተባለውን እግረኛ ገጭቶ በመግደል፣ ካዛንችስ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ አቅጣጫ ሸሽቶ ማምለጡን የመሰከሩ ሲሆን፤ በተለምዶ አደጋው በደረሰበት አካባቢ በፀጥታ ጥበቃ ላይ የነበረው የፖሊስ ሠራዊት ባልደረባ ነው። የዓቃቤ ሕግ ምስክር ስለሁኔታው ሲያስረዳ፣ ተሽከርካሪውን አደጋ ባደረሰበት ቦታ በ20 ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ተከታትሎ ወደ መኪናው በ5 ሜትር በመጠጋትም፣ በአካባቢው በነበረው ከፍተኛ ብርሃን (ፓውዛ) በመታገዝ የመኪናውን የሠሌዳ ቁጥር መያዝ ስላልቻለ፣ ለ2ኛው የዓቃቤ ሕግ ምስክር በፖሊስ የሰጠው የምስክርነት ቃልም ይህንን የሚደግፍ ወይም የሚያጠናክር ነው።

 

ከተከሳሽ ቃል ከተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮችና በዓቃቤ ሕግ በኩል ከቀረቡት ምስክሮች አነጋገር የምንረዳው እውነታ የተከሳሽ ንብረት የሆነውና የሰሌዳ ቁጥሩ 2-59869 አደጋ ደረሰ በተባለበት ጊዜ ሲያሽከረክር የነበረው ተከሳሽ መሆኑን ነው።

 

ተከሳሽም ሆነ መከላከያ ምስክሮቹ የሰጡት የአስረጂነት ቃል፣ የቦታና የጊዜ ልዩነት ካልሆነ በቀር መኪናው ማን ሲያሽከረክረው እንደነበረ አጠራጣሪ ሆኖ አልተገኘም።

 

ተሽከርካሪው በፍጥነት እየተሽከረከረ በነበረበት አኳኋን፣ አራት ኪሎ ፊት በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በዓቃቤ ሕግ ምስክሮች መታየቱ ይኸው ተሽከርካሪ ሰው ገጭቶ በመግደል ማምለጡንና ምስክሮቹ አልተነገረም ተከሳሽ ከነርሱ ተለይቶ መኪናውን ሲያሽከረክር በነበረበት ወቅት አደጋውን ማድረሱን የሚያስተባብል አይሆንም።

 

ከዚህም በተጨማሪ ፍ/ቤቱ ከጥቅምት 6 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ቀርቦ ከተመለከትነው ተከሳሽ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለትራፊክ መቆጣጠሪያ መምሪያ በሰጠው የተከሳሸነት ቃል እንደገለፀው፣ በ4ኛው የዓቃቤ ሕግ ምስክር እንደተነገረው ተከሳሽ አደጋው ደረሰ በተባለበት ጊዜና ቦታ፣ የመንጃ ፈቃድ ሳይኖረው፣ የተጠቀሰውን መኪና እያሽከረከረ ማለፉን በራሱ በተከሳሹም ጭምር መረጋገጡ ሲታይ፣ መከላከያ ምስክሮቹ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. እስከ ለሊቱ 9 ሰዓት ድረስ መስቀል ፍላወር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አምሽተናል በማለት የሰጡት የምስክርነት ቃል በተለይ በተጠቀሰው ሰዓት፣ በግምት የተሰጠ ነው ከመባል በቀር፣ በዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ከተነገረው ውጭም ሆነ ተከሳሽ ራሱ ከምርመራ ክፍሉ ከሰጠው ቃል፣ አንፃር ሲታይ፣ የመከላከያ ምስክሮች ቃል በዚህ ረገድ የዓቃቤ ሕግ ክስና ማስረጃ አስተባብሏል ለማለት አይቻልም።

 

4ኛው 6ኛው 7ኛው እና 14ኛው መከላከያ ምስክሮች የሰጡትን የምስክርነት ቃል ሙሉ በሙሉ ያተኮረው፣ ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሉ የተሰጠውን የሟች የአስክሬን የምርመራ ውጤት ምስክር ወረቀት ነው።

 

ይህ ፍርድ ቤት ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ በሰጠው ብይን እንደተመለከተው የተጠቀሰው የአስከሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት የሚያረጋግጠው፣ አስከሬኑ መቼ ወደ ሆስፒታል ለምርመራ እንደገባና፣ መቼ ምርመራ እንደተደረገለት የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በአንድ በኩል አስከሬኑ ለምርመራ የገባበት ቀን ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. እንደሆነና፣ ምርመራ የተደረገውም ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. እንደሆነ የሚገልጽ ኅዳር 4 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሆስፒታሉ የተሰጠ የአስከሬን ምርመራ ውጤት በዓቃቤ ሕግ በኩል በማስረጃነት በመቅረቡ አስከሬኑ ወደ ሆስፒታሉ ለምርመራ የገባበት ቀን ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑንና ምርመራው የተደረገበት ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን የሚገልፅ ሰኔ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. ከሆስፒታሉ ታርሞ የተሰጠ የአስከሬን ምርመራ የምስክር ወረቀት በዓቃቤ ሕግ መቅረቡ አከራካሪ ሆኖ ስለተገኘ፣ ለተከሳሽ ፍትህ አሰጣጥ ሲባል መጣራቱ አስፈላጊ ስለነበር፣ ከሆስፒታል የተላከ የአስከሬን ምርመራ ባለሞያ፣ የአሁኑ የተከሳሽ ምስክር ቀርቦ በሆስፒታሉ ታምኖበት ትክክለኛ ማስረጃ ሰኔ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. ከሆስፒታሉ ታርሞ የተሰጠው ሟች ደጉ ይበልጣል ለአስከሬን ምርመራ ሆስፒታል የገባው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ሲሆን፣ የአስከሬን ምርመራ የተደረገለት ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሆስፒታሉ የተሰጠው የሟች አስከሬን የምርመራ ምስክር ወረቀት የቀን ስህተት የነበረበት መሆኑንና፣ እርማቱ የቀን እንጂ የይዘት አለመሆኑን፣ ለዚሁ ፍ/ቤት ቀርቦ አስረድቷል ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ ከሌሎችም ማስረጃዎች ጋር አመዛዝኖ፣ ከሆስፒታሉ ታርሞ የተሰጠው የአስክሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት በማስረጃነት ተቀብሎት ይላካል ሲል ብይን ሰጥቶበታል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተከሳሽ በኩል በመከላከያ ምስክርነት እንዲሰሙለት ተቆጥረው፣ ከፍ ብሎ የተጠቀሰው የዳግማዊ ምኒልክ የሕክምና ባለሞያዎች ኃላፊዎች ከሰጡት የምስክርነት ቃል የሚከተለው ይገኝበታል።

 

ምስክሮቹ በሆስፒታሉ በተለያዩ የሞያ ክፍሎች ኃላፊነቶች ተመድበው እንደሚሠሩ፣ ሕዳር 4 ቀን 1999 ዓ.ም. ስለሟች ደጉ ይበልጣል ከሆስፒታሉ በተሰጠው የአስከሬን ምርመራ የምስክር ወረቀት ላይ፣ በተለይ 4ኛው የመከላከያ ምስክር በነበረው ኃላፊነት መፈረሙንና፣ ሲፈርም ስህተቱን ባያነበውም አሁን ግን ስህተት መሆኑን እንደሚያምን የዚህ ዓይነቱ የቀን ስህተት ሲያጋጥም እርማት ማድረጉ የሆስፒታሉ የተለመደ አሰራር መሆኑን የመሰከረ ሲሆን፣ ሌሎች የመከላከያ ምስክሮች በተጠቀሰው ማስረጃ ላይ የቀን ስህተት እንደተከሰተና፣ ስህተቱን ማወቅ የተቻለበት ምክንያትም የሟች ደጉ ይበልጣል አስከሬን ወደ ሆስፒታሉ የገባው፣ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ15 ደቂቃ እንደሆነ፣ በአስከሬን መግቢያ ቅፅ ላይ ከተሞላው ዋናው የማስረጃ ምንጭ ከሆነው የፖሊስ ፓድ መረዳት በመቻላቸውና፣ በወቅቱ ሥራ ላይ የነበረችው የአስከሬን መርማሪ ሐኪም ቀኑን ከፖሊስ ፓድ ወይም የአስክሬን መግቢያ ቅፅ ወደ ዋናው መዝገብ ስትገለብጥ የፈጠረችው የቀን ስህተት መኖሩ፣ ማለትም ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. አስከሬኑ ወደ ሆስፒታሉ እንደገባና ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ምርመራ እንደተደረገለት የሚያመለክተው የምስክር ወረቀት፣ ከፖሊስ ፓድ ጋር ሲነፃፀር ወይም በማጣጣም ከፖሊስና ዓቃቤ ሕግ የተስተካከለ ማስረጃ እንዲሰጣቸው በጠየቁበት ጊዜ መሆኑን ገልፀው፤ አስክሬኑ ወደ ሆስፒታሉ ለምርመራ ወደ ሆስፒታሉ የገባበት ቀን ጥቅምት 23 ቀን 1999 መሆኑን ከሚያስረዳው የፖሊስ ፓድና አስከሬኑ ምርመራ የተደረገበት ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን ከሚያመለክተው ዋናው የአስከሬን ምርመራ መዝገብ በማየት የሟች የአስከሬን ምርመራ ወደ ሆስፒታሉ የገባው፣ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑንና ምርመራ የተደረገበት ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን በማረጋገጥ፣ ሰኔ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ለትራፊክ መቆጣጠሪያ ምርመራ መምሪያ የተስተካከለ ማስረጃ መሠጠቱን መስክሯል።

 

4ኛ መከላከያ በበኩሉ፣ ያስተካከለው የምስክር ወረቀት ላይ መፈረሙን ገልፆ የተሳሳተው የምስክር ወረቀት ሲሰጥ በቦታው አለመኖሩን፣ አስከሬኑም ያልመረመረ በመሆኑ ስለ ጉዳዩ አዲስ ቢሆንም ቀደም ሲል ምርመራውን ያደረገቸው ሐኪም ተክቶ ስለሚሠራ ብቻ መፈረሙን፣ የውጭ ሀገር ዜጋ እንደመሆኑ መጠን በሀገሩ አሠራር ሟች የሞተበትን ቀን በግምት ካልሆነ በትክክል ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልፆ፣ አንድ ሰው ሕይወቱ ያለፈበትን ቀን ለማወቅ ባለሞያው በአካል መገኘት እንደሚያስፈልግ የሀገሩን ተሞክሮ አውስቶ በተያዘው ጉዳይ ድጋሚ የአስከሬን ምርመራ አለማድረጉን ገልጿል።

 

በመሠረቱ ሆስፒታሉ ሟች የሞተበትን ምክንያት እንደሚያረጋግጥና፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት እንዲሰጥ በምርመራ ክፍሉ ተጠየቀ እንጂ፣ ሟች በደረሰበት አደጋ ምክንያት ለሞት እንደበቃ የሚያስረዳ ማስረጃ ከሰጠ በኋላ፣ ይኼን ጉዳይ በተመለከተ የቀረበ ክርክር የለም። ክርክሩ የነበረው ሟች የሞተበትን ምክንያት በሚመለከት ሳይሆን የሟች አስክሬን ለምርመራ ሆስፒታል የገባበትን ቀንና ምርመራ የተደረገበትን በማመለከት ነው ስለሆነም አከራካሪ የሆነው የቀን ጉዳይ ስለሆነ ሆስፒታሉ የተጠየቀው የሟች አስከሬን መቼ ወደ ሆስፒታሉ እንደገባ ምርመራ መቼ እንደተደረገለት ስለሆነ፣ በዚሁ ጥያቄ መሠረት ይህንኑ ለማረጋገጥ የሚሠጠው ማስረጃ ተያያዥነት ካላቸው ተገቢ ሠነዶች በማነፃፀር የሚሠጥ እንጂ አስከሬኑ እንደገና መመርመር አስፈላጊ አይሆንም፤ በተከሳሽ በኩልም ሟች የሞተበት ምክንያት ለማረጋገጥ አስክሬኑ እንደገና እንዲመረመር የቀረበ ጥያቄ የለም። በመሆኑም ባለሞያው አስክሬኑን እንደገና አልመረመረኩም ማለቱ ለጉዳዩ አከራካሪ ባልሆነ ነጥብ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ አስከሬኑ እንደገና ባለመመርመሩና በተያዘው ጉዳይ ላይ የሚያመጣው የተለየ ውጤት አይኖርም።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሌሎች የመከላከያ ምስክሮች በቀረቡት የሆስፒታሉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች እንደተገለፀው፣ በሀገራችን አሠራር አንድ የአስከሬን ምርመራ የምስክር ወረቀት አስክሬኑ ለምርመራ የገባበትን ቀን እንዲሁም ለሞት የበቃበትን ምክንያት ማመልከት እንደሚገባው በማስረዳት፣ የቀን ስህተት ሲያጋጥም ዋናው ይዘቱ ሳይቀየር፣ ስህተቱን ማስተካከል እንደሚቻልና፣ በዚሁ መሠረት በጉዳዩ የተጠቀሰው የሟች አስከሬን የምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት ሰኔ 13 ቀን 2000 ዓ.ም. በትራፊክ መቆጣጠሪያና ምርመራ መምሪያ የተፃፈ መሆኑን መስክረዋል።

 

14ኛው የመከላከያ ምስክርም ቢሆን፣ የሆስፒታሉን አጠቃላይ አሠራር ከነዚህ ምስክሮች በተለየ ሁኔታ አልገለፁም። የነዚህ የመከላከያ ምስክሮች ደግሞ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ የሚያጠናክር ነው ከመባል በስተቀር፣ የዓቃቤ ሕግን ክስና ማስረጃ አስተባብሏል ለማለት የሚያስችል አይደለም። በተለይም ጥቅምት 23 1999 ዓ.ም. አደጋው ደረሰ በተባለበት ቦታ ሥራ ላይ የነበረው፣ በተ.ቁ. 9 የመከላከያ ምስክር ሆኖ የቀረበውና፣ አንደኛው የዓቃቤ ሕግ ምስክርና ሌሎችም ምስክሮች እንዳስረዱት ሟች በመኪና ተገጭቶ ወዲያውኑ ሕይወቱ ማለፉን፣ ይኸው ቀንና ሰዓት ደግሞ የአደጋውን ቦታ በሚያመለክተው ፕላን ላይም ተመዝግቦ የሚገኝ በመሆኑ፣ አስክሬኑ ወደ ሆስፒታው ሲወስድም በሁሉም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የተነገረ በመሆኑ፣ እንዲሁም በማግስቱ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. አደጋ ያደረሰው መኪናና ተከሳሽ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መረጋገጡ ማስረጃው እርስ በርሱ በማገናዘብ ስንመዝነው፣ የተከሳሽን ወንጀል ያረጋገጠና የተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ ያልተስተባበለ መሆኑ ነው። ከፍ ሲል እንደተገለፀው ሟች በተከሳሽ ተሽከርካሪ ተገጭቶ ሕይወቱ ያለፈበት ቀን፣ ጥቅምት 23 ቀን ከሌሊቱ 7፡10 መሆኑ በዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ሲሆን፣ ይህን ጭብጥ ያስተባብላሉ ተብለው ቀርበው የተሰሙ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች የምስክርነት ቃል አልተስተባበለም በተከሳሽ በኩል የተለየ የመከላከያ ማስረጃ አልቀረበም። ማስረጃዎች የሚመዘኑት አንዱ ከሌላው ጋር በሚኖራቸው ትስስር አንፃር በመሆኑ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል ሆስፒታሉ ከሰጠው የተስተካከለ ወይም የታረመው የአስከሬን ምርመራ ውጤት የምስክር ወረቀት ተደጋጋፊነት ያለው ሆኖ በመገኘቱ ሠነዱ ውድቅ የሚደረግበት ምክንያት አልተገኘም።

 

12ኛ የመከላከያ ምስክር አደጋውን ያደረሰውንና፣ ተገጭቶ የተያዘውን መኪና የቴክኒክ ምርመራ ያደረገው የፖሊስ አባል ሲሆን፣ በቴክኒክ ምርመራ ውጤቱ ተከሳሸ አለመፈረሙንና የቴክኒክ ምርመራ የተደረገው ወይም አደጋው ደረሰ ከተባለበት ቀን ዘግይቶ መሆኑን የሰጠው የምስክርነት ቃል፣ በተከሳሽ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች ከማስተባበል አኳያ ጠቀሜታ ያለው አይደለም።

 

የተከሳሹን የሠነድ መከላከያዎች በሚመለከት፣ ከዳግማዊ ምኒልክ የተሰጡት የአስከሬን ምርመራ ምሥክር ወረቀቶች፣ ከፍ ብሎ ላነሳነው ጭብጥ በተሰጠው ትችት የሚካተቱት ናቸው የተከሳሸ ፓስፖርት ቪዛና፣ የሀገር ውስጥ መመለሻ ማስታወሻ ክርክር ያልቀረበበት ስለሆነ ታልፏል።

 

ታምራት ዱላ የተባለው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ለፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ አደጋ ያደረሰውን መኪና የሠሌዳ ቁጥር ባለመጥቀሱ የሰጠው የምስክርነት ቃል ዓመኔታ የለውም በሚል የቀረበውን ሠነድ በሚመለከት፣ ምስክሩ ፍ/ቤት ሲመሰክር ከተከሳሽ ጠበቃ ይህን አስመልክቶ መስቀለኛ ጥያቄ ቀርቦለት ለፖሊስ ቃሉን በሚሰጥበት ጊዜ የመኪናውን የሠሌዳ ቁጥር ባለመጠየቁ እንጂ ምላሽ ለመስጠት ይችል እንደነበር ለፍ/ቤቱ በመናገሩ እና በሠነዱ ላይ ይህ ጥያቄ ቀርቦለት፣ ለፍርድ ቤት የገለፀ መሆኑን፣ ፍ/ቤት ቀርቦ የሰጠው የምስክርነት ቃል አመኔታ የለውም ተብሎ የቀረበው መከራከሪያ ተቀባይነት አያገኝም።

 

በተ.ቁ 7510/ወ/82 ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. የትራፊክ መቆጣጠሪያ መምሪያ፣ ለፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት፣ ለልደታ ምድብ ችሎት በፃፈው የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማመልከቻ ላይ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች አደጋ ያደረሰውን መኪና ሠሌዳ ቁጥር አያውቁም ነበር በማለት የተነሳው ክርክር የሠነዱን ሙሉ ይዘት ካለመረዳት እንደሆነ እንጂ በሠነዱ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ተሽከርካሪው ሟችን ገጭቶ ሲያመልጥ በቦታው ተመድበው ሥራ ላይ የነበሩት የፖሊስ ሠራዊት አባላት ማየታቸውን ተመልክቷል። እነዚህም ቃላቸውን ሲሰጡ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀበት ይኸው ሠነድ፣ የአደጋ አድራሹን ስምና የተሽከርካሪውን የሠሌዳ ቁጥር እንዲሁም አደጋ የደረሰበት ቦታና ጊዜ፣ የአደጋውን አፈፃፀም ያመለከተ በመሆኑ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የመኪናውን የሰሌዳ ቁጥር አያውቁም ነበር ለማለት የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት አይደለም። ስለሆነም ከላይ በዝርዝር በተገለጹት የፍሬ ነገር ምክንያቶች፣ ተከሳሽ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ አስተባብሏል ለማለት ስላልተቻለ፣ ተጠቅሶ በቀረበበት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543 (3) ቁጥር 279/1956 አንቀጽ 5/4 እንዲሁም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 575(2) ስር ጥፋተኛ ነው ብለን በወ.መ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 149(1) መሠረት ወስነናል።


 

ከላይ የሰፈረው ውሳኔ በችሎቱ ተነቦ እንዳለቀ በችሎቱ ውስጥ ጉምጉምታ ተጀመረ። ዓቃቤ ሕግም ከፍርድ ቤቱ ለተጠየቀው የቅጣት ሃሳብ ምንም እንኳን ተከሳሹ ቀደም ሲል በወንጀል የተመዘገበ ሪከርድ ባይኖርበትም የፈጸመው ወንጀል ተደራራቢ በመሆኑ እሱንና ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል ቅጣት እንዲቀጣለት ጠየቀ።

 

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፤ የቅጣት ማቅለያ ሃሳብ ሲጠየቁ አቶ አምሃ በድሉ የተባሉት ሁለተኛው ጠበቃ፤ በክሱ “ጥፋተኛ አይደለንም” በሚል ሲከራከሩ በመቆየታቸው ምክንያት፣ የሚያቀርቡት ምንም የቅጣት አስተያየት አለመኖኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ።

 

ቴዲ አፍሮ በነዚህ አንቀጾች ጥፋተኛ በተባለበት በዚያች ቅጽበት፤ መረጋጋት አቅቶት ከአንደኛው ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ጋር ሲነጋገር የነበረ ሲሆን፤ ከፍርድ ቤት ሲወጣም “እግዚያብሔር ይፈርዳል” ሲል ተደምጧል።

 

 

ተያያዥ

 

Make a Free Website with Yola.