Some things about Tedy Afro

በመጨረሻ ነፃ ሆነ - Free at last PDF Print E-mail

Teddy Afro ቴዲ አፍሮ- እኔም ከቴዲዬ ጋራ አብሬ ተፈትቻለሁ - የቴዲ እናት

- መልካም ዕድል ይግጠምህ! - ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም

- አመክሮው በ2 ዓመት ገደብ ተሰጥቶታል

- አድናቂዎቹ ደስታቸውን ገለፁ

ጽዮን ግርማ

የልደታው የፌደራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ መደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚዘጉበት ወቅት በመሆኑ ፀጥታ ነግሷል። በከፍተኛው ፍርድ ቤት አሥራ ስድስት የወንጀልና አሥር የፍትሐብሔር መደበኛ ችሎቶች ሲኖሩ፤ ከሦስቱ መደበኛ የወንጀልና ተረኛ ችሎቶች በስተቀር የሁሉም ብረት በሮች ክርችም ተደርገው ተዘግተዋል።

 

የመደበኛ ችሎት ዳኞች ለነሐሴ የቀጠሩትን መዝገብ ለማጠናቀቅ ካልሆነ በስተቀር በችሎት አይሰየሙም። እነሱም ቢሆኑ ጠዋት እንጂ ከሰዓት በኋላ እምብዛም አይገኙም። መግቢያው በር ላይ ባሉት አግዳሚዎች አለፍ አለፍ ብለው ከተቀመጡት ጥቂት ባለጉዳዮች በስተቀር ማንም በግቢው የለም - ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ።

 

ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል አካባቢ ማንም ያላስተዋላት አንዲት ቶዮታ ፒክአፕ የፖሊስ መኪና ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ ሰተት ብላ ገባች። በመኪና ተጭነው ከመጡት የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ውስጥ አንድ ኃላፊ በእጁ ወረቀት ይዞ፣ በጓሮ በኩል ወዳለው የዳኞች ቢሮ አዘገመና የስምንተኛ ወንጀል ችሎት ጽ/ቤትን በር አንኳኩቶ ገባ። ከደቂቃዎች በኋላ ባዶ እጁን እየተቻኮለ ወደ መኪናዋ አመራ።

 

አሥራ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ መዝገብ ከመዝገብ ቤቱ በሬጅስትራሩ አማካኝነት ወደ ችሎት ተላከ፤ የችሎቱ ፖሊስ ችሎቱን እንዲያሰይም ተጠራ። ወደ መኪናው የሄደው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ፖሊስና የሥራ ኃላፊ በመኪና ይዘውት የመጡትን እስረኛ በፖሊስ አሳጅቦ ወደ ችሎቱ አስገባ።

 

ችሎቱ ባዶና ፀጥታ የሰፈነበት ነበር። ድምፅ ቀራጩ ሳጥኑ ውስጥ ቁጭ ብሎ ካሴቱን ያስተካክላል። ሁለት የችሎት ፖሊሶች ችሎቱን ለማሰየም በተጠንቀቅ ይጠባበቃሉ። ከማረሚያ ቤት እስረኛውን አጅበው የመጡት አራት ፖሊሶችም እንዲሁ በማመልከቻ ጽፈው ያቀረቡት ጉዳይ ላይ ዳኛው የሚሰጡትን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የችሎቱ ተከታታይ አግዳሚ ወንበሮች ግን ባዷቸውን ነበሩ።

 

አንድ ዓመት ከአራት ወራት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሲታሰር ከ20 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ተመላልሷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ከቀረበበት ቀን አንስቶ እስከ መጨረሻ የሰበር ውሳኔ ድረስ ችሎቱ በሰዎች ሳይጨናነቅ ጉዳዩ ታይቶ አያውቅም። ያለ ጠበቃም በዳኛ ፊት ቀርቦ አያውቅም - አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)።

 

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን፤ ዳኛው ረጋ ባለ መንፈሥ ወደ መቀመጫቸው አምርተው ተሰየሙ። ያለመንጃ ፍቃድ በማሽከርከር፣ ሰው በመግጨት ዕርዳታ ሳያደርግ በማምለጥ፣ ለሞት መዳረግ በሚል የቀረበበትን ክስ ለመጀመሪያ ጊዜ ባነበቡለትና፤ በተከሰሰበት ወንጀልም የመጀመሪያውን የጥፋተኝነት ውሳኔ፣ የስድስት ዓመት እስር እና የ18 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት በሰጡት ዳኛ ልዑል ገብረማሪያም ፊት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንም ከተቀመጠበት አግዳሚ ወንበር ላይ ተነስቶ ተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ቆመ። ከዳኛውና ድምፅ ቀራጩ በስተቀር አርቲስት ቴዎድሮሰ ካሳሁን፣ ችሎት አስተባባሪውና ስድስት ፖሊሶች ብቻ በባዶው ችሎት ውስጥ ቆመው ውሳኔውን በፀጥታ መጠባበቅ ጀመሩ።

 

ዳኛ ልዑል ቀጠሉ፤ “ቴዎድሮስ ካሳሁን ለማረሚያ ቤት የጻፍካቸው ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውናል። በማረሚያ ቤት በነበረህ ቆይታ መልካም ፀባይ እንዳሳየህ የሚያረጋግጠው የማረሚያ ቤቱ ፎርምም ደርሶናል” ካሉ በኋላ፤ በማረሚያ ቤቱ ምን ትምህርት እንዳገኘ ላቀረቡለት ጥያቄም፤ አርቲስት ቴዎድሮስ በእስር ቤት በነበረው ቆይታው የሕግን የበላይነት አውቆ መረዳቱን አረጋገጠላቸው። ለማረሚያ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤም፤ “አመልካች ቴዎድሮስ ካሳሁን ግርማሞ፤ ጉዳዩ በአመክሮ የምፈታበት ጊዜ ስለደረሰ እንድገመገም ስለመጠየቅ ይሆናል።

 

“ይኸውም በተከሰስኩበት የወንጀል ክስ ክርክር ሲደረግበት ቆይቶ፤ የፌ/ከ/ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ አድርጐኝ የ6 ዓመትና የ18 ሺህ (አሥራ ስምንት ሺህ ብር) መቀጮ መወሰኑ ይታወቃል። ሆኖም የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ደግሞ ይህንን የቅጣት ውሳኔ በማሻሻል፣ ውሳኔውን በመቀነስ በ2 ዓመት እስራት እንድቀጣ ውሳኔውን በማሻሻል ትዕዛዝ ያስተላለፈልኝ ሲሆን፤ እኔም በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ሆኜ ሁለት ሦስተኛውን በመታሰሬ፣ የሕግ የበላይነትን የተማርኩኝ፤ የወንጀልን አስከፊነት የተረዳሁኝ ሲሆን፤ ከማረሚያ ቤቱ በምፈታበት ጊዜ ከኅብረተሰቡ ጋር ሠላማዊ ኑሮዬን የምቀጥል ሲሆን፤ ማረሚያ ቤቱ አመክሮ እንዲሰጠኝና ከእስር እንድፈታ ስል በማክበር አመለክታለሁ።” በማለት ማረጋገጡን አስታውሰው፤ “ማንም ዜጋ የሀገሩን ሕግ አክብሮ መኖር አለበት፤ አንተም ከዚህ በኋላ የሀገሪቱን ሕግ አክብረህ መንቀሳቀስ ይጠበቅብሃል” ሲሉ ምክር ለግሰውታል።

 

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ለማረሚያ ቤቱ ከፃፈው ደብዳቤና ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤቱ ካቀረበው ማመልከቻ መረዳት እንደሚቻለው በእስር ቆይታው መልካም ፀባይ በማሳየቱና ከስህተቱ መታረሙን የገለፀ በመሆኑ በሕጉ ላይ፤ አንድ እስረኛ ከተፈረደበት የእስራት ዘመን ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሦስተኛውን እስር ቤት ካሳለፈ በኋላ አመክሮ ሊያሰጡት የሚችልባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላቱ ተረጋግጦ ከእስር ሊለቀቅ ይችላል በሚል በተቀመጠው ሕግ መሰረት፤ ከሁለት ዓመት የእስራት ቅጣት አንድ ዓመት ከአራት ወራት በመታሰሩ የስምንት ወራት አመክሮው ፀንቶለት፤ በሁለት ዓመት ገደብ እንዲፈታ ወስነውለታል።

 

ዳኛው አያይዘው፤ “ጥፋት ትፈጽማለህ ብለን ባንገምትም፣ አያድርገውና በዚህ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ ጥፋት ፈጽመህ ብትገኝ፣ በአመክሮ የተሰጠህ የስምንት ወራት የእስራት ቅጣቱ መብት ተነስቶ፣ እስራቱ ተፈፃሚ ይሆናል” በማለት ከገለጹ በኋላ፤ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረው ከሐሙስ ነሐሴ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ከእስር እንዲለቀቅ መፍቻ ለማረሚያ ቤቱ ይፃፍ የሚል ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ “መልካም ዕድል ይግጠምህ!” ሲሉ መልካሙን ተመኝተው አሰናብተውታል።

 

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በዛች ሰዓት ፍርድ ቤት ስለመቅረቡ አንድም የሚያውቅ ሰው ባለመኖሩ፤ ሁሌም ከችሎት ሲወጣ የለመደው የአድናቂዎቹ መልካም ምኞትና የፍርድ ቤት ግርግር አልገጠመውም። በግቢው ውስጥ ዘና ብሎ በመቆም የማረሚያ ቤት ፖሊሶች፣ የዳኛውን ትዕዛዝ አስጨርሰው እስኪመጡ ከጥቂት አጃቢዎቹ ጋር መጠባበቅ ጀመረ።

 

ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መፈቻው በመጠናቀቁ ፒካፕዋ መኪና ይዛው ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተፈተለከች።

 

በማረሚያ ቤቱ ግቢ

የማረሚያ ቤት ምንጮቻችን እንደጠቆሙት፣ አርቲስቱ በዚህ ሣምንት ውስጥ እንደሚፈታ አስቀድሞ ግምቱ ስለነበረው ዕቃዎቹን ወደ ቤተሰቦቹ አስቀድሞ ልኳል። በእስር ቤት ውስጥ ይጠቀምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችንም ለእስረኞች አከፋፍሏል። ከቤተሰቦቹና ከወዳጅ ዘመዶቹ ይገቡለት የነበሩትን በርካታ መጻሕፍት ለማረሚያ ቤቱ መጻሕፍት ቤት በስጦታ አበርክቷል። የቀሩትን ጥቂት ዕቃዎች በዕለቱ በአንድ ጓደኛው ልኳል። ማረሚያ ቤት ደርሶ የፍቺው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ሰማያዊ የስፖርት ቱታ በቀይ ቲሸርት ለብሶና የስፖርት ጫማ ተጫምቶ እስረኞቹን መሰነባበት ጀመረ።

 

የማረሚያ ቤት ምንጫችን ሁኔታውን ሲገልፁልን፤ “ቴዲ በእስረኞቹ ዘንድ የተወደደ ነው። እሱም ለሰው ከፍተኛ ፍቅር አለው፤ በተለይ በእስር በነበረው ቆይታው ለፋሲካና ለዘመን መለወጫ ባሉት በዓላት ለእስረኞች ሰንጋ አርዶ እስከማብላት የደረሰ የማይረሱ ውለታዎችን ውሏል። በዚህና በሌሎች ባሳለፋቸው ጥሩ ጊዜያቶች የተነሳ በደስታ ስሜት ነበር እስረኞቹ የሸኙት” ብለውናል።

 

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት መግቢያ በር ላይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አድናቂዎቹ መፈታቱን ለመመልከት በር ላይ ሆነው መጠባበቅ የጀመሩት ረቡዕ ዕለት ጀምሮ ቢሆንም ሐሙስ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ከ45 ደቂቃ አካባቢ አንድ ሰው ከግቢው ይዛ የወጣችውን ሚኒባስ የተመለከቷት አይመስሉም።

 

ሚኒባሷ በቃሊቲ “ሃያ ሁለት” እየተባለ በሚጠራው ሰፈር መንገዷን ቀጠለች። እኛም ተከተልን። በኋላ ለመረዳት እንደቻልነው የቴዲ አፍሮ ወላጅ እናት መኖሪያ ቤቷን የቀየረችው እርሱ እስር ቤት ከገባ በኋላ በመሆኑ፣ የእናቱ ቤት የት እንደሚገኝ አያውቅም ነበር። በዚህም ምክንያት ነው መኪናዋ እዛው “ሃያ ሁለት” እናቱ ቤት አቅራቢያ ወደሚገኘው የአክስቱ ቤት ያመራችው። ቴዲ ከመኪናው ሳይወርድ የእናቱን ቤት የሚያሳይ ሰው መኪናው ላይ ተጭኖ ወደ እናቱ ቤት ተወሰደ።

 

ቴዲ ከመኪናው ወርዶ ወደ ግቢው ሲገባ ቤተሰቦቹ እጅግ ተደናግጠው ነበር። እናቱ ጥላዬ አራጌ (ራዬ) አንገቱ ላይ ተጠምጥማ በሳግ ማንባት ጀመረች። ድንጋጤው ይመስላል ከደስታ ጩኸትና እልልታ ይልቅ ግቢው በፀጥታ ተዋጠ። አንዲት ድንክ ውሻ ግን እየጮኸች ቴዲ ላይ ተንጠለጠለች - ውሻዋ ከስምንት ዓመት በፊት ቴዲ ከጓደኛው ወስዶ ያሳደጋት ስትሆን፤ አንድ ዓመት ከአራት ወራት ተለያይተው መገናኘታቸው ነው - ቴዲና ውሻዋ።

 

ቤተሰቡ ከድንጋጤ ተላቆ ደስታውን ለመግለጽ ከ10 ደቂቃ በላይ ወስዶበታል። ቤቱን ከጐበኘና ከመታጠቢያ ቤት ከወጣ በኋላ ቤቱ መፈታቱን በሰሙ ጓደኞቹና ወዳጅ ዘመዶቹ ተሞላ። ሻምፓኝ ከፍቶ ከእናቱ ጋር ብርጭቆውን በማጋጨት ደስታውን ገለፀ። ወዳጅ ዘመዶቹን በመቀበል ተቃቅፎ ሲሳሳም አመሸ። ከየአቅጣጫው የሚደወለውን ስልክ ማስተናገድም ሌላው የቴዲ ሥራ ነበር። አንዳንዴም በሁለት ጆሮዎቹ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለማስተናገድ ተገድዶ ነበር።

 

ቴዲ በዚህ ሁሉ ግርግር መካከልም “ግቡ ራት ብሉ፣ የሚጠጣ ነገር ስጧቸው፣ … ቁጭ በሉ! …” እያለ እንግዶቹን ማስተናገድ አልዘነጋም። እስከ ምሽቱ ስድስት ሰዓት ድረስም ደስታውን ለመግለጽ የሚመጣው ሰው ቁጥር አልቀነሰም። አንዳንድ አድናቂዎቹ ጉንጩን ስመው ደስታቸውን ከመግለጽ ይልቅ እያለቀሱ እግሩ ላይ ሲደፉ ታይተዋል።

 

ከአጥሩ ውጪ ያለው አካባቢ በመኪና ተጨናንቋል። ከመኪናው እየወረደ ወደ ግቢው የሚገባው ሰውም በፊቱ ላይ ያለማመን ስሜት ይነበብበታል።

 

ከቅርብ ቤተሰብ ውጭ ያለው፤ ጓደኛና ወዳጅ ዘመድ፣ ግቢውን ለቆ የወጣው ከእኩለ ለሊት በኋላ ነበር። ቴዲም ከቤተሰቦቹ ጋር ሲጫወት አምሽቶ ሲነጋጋ ጋደም ማለቱን በትናንትናው ዕለት ለቃለ ምልልሱ ስናገኘው አጫውቶናል።

 

የቅዳሜና እሁድ ጠያቂዎቹ

የቴዲን መታሰር ዜና የሰሙ ወጣቶች ከያሉበት ወደ ፍርድ ቤት ማምራት የጀመሩት ከአንድ ዓመት ከአራት ወር በፊት ነበር። ፍርድ ቤት መሄድ ብቻ እርካታን አልሰጥ ሲላቸው ወደ እስር ቤት ማምራት ጀመሩ። የቴዲ የመጀመሪያዎቹ የእስር ወራት ጉብኝት የሚፈቀደው ቅዳሜና እሁድ ከስድስት እስከ ሰባት ሰዓት ብቻ በምዝገባ በመሆኑ ማረሚያ ቤቱ እንዲገቡ በሚፈቅደው የጠያቂዎች ቁጥር መሰረት፤ ሥርዓት ባለው መልኩ ጠያቂዎች እንዲስተናገዱ ከምዝገባ ጀምሮ ቤተሰቡን መርዳት ጀመሩ። ከዚያም የቴዲ ቋሚ ጠያቂ በመሆን ማጽናናታቸውን ቀጠሉ። የእነዚህ ወጣቶች ቁጥር ወደ ሃያ የሚጠጋ ቢሆንም ቋሚ ጠያቂዎቹ ከሰባት የሚበልጡ አልነበሩም።

 

የቴዲ መጠየቂያ ሰዓት በመደበኛው ዘወትር ቅዳሜና እሁድ ጠዋትና ከሰዓት ሲደረግ የቴዲ ጠያቂዎች ቴዲን ብቻ ብለው የሚመጡ አልነበሩም። ሌላ እስረኛ ለመጠየቅ የሚመጡ በርካታ ጠያቂዎች ቴዲ ወደ ታሰረበት በመሄድ ለመጨበጥ ይሰለፉ ነበር። ይህ ሁኔታ ግርግር እንዳይፈጥር በመከታተልና ሰዎች ረጋ ብለው እንዲሄዱ ሳይታክቱ ጥበቃ በማድረግ የአድናቆታቸውን አጋርነት አሳይተውታል።

 

የ27 ዓመቱ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴ አሠልጣኝ ወጣት ሄኖክ ብርሃኑ፤ ከወጣቶቹ አንዱ ነው። ቴዲ ከመታሰሩ በፊት አንድ ቀን ቤተክርስቲያን ውስጥ አግኝቶት ከመጨበጥ ውጭ በአካል አይቶት አያውቅም። መታሰሩን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ እስከሚፈታበት የመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ቋሚ ጠያቂው ሆነ። “ሰው ከተዋደደ ጓደኝነት መመስረት ይችላል፤ እሱን ብለን ስንሄድና ተደጋጋሚ ጊዜ ስንተያይ ጓደኝነት መሰረትን። የተገናኘነው የቴዲ አድናቂ በመሆናችንና እሱን የመጠየቅ፣ የማበረታታትና የማጽናናት ዓላማ ስለነበረን እስኪፈታ ድረስ ሄደን እንጠይቀው ነበር። መፈታቱን ማመን አልቻልንም፤ እስካሁን ደስታው አልወጣልንም” ብሎናል።

 

ፍሬሕይወት ይልማ፣ ጥላሁን አበበ፣ ሣሙኤል ሙሉጌታ፣ መለሰ መኮንን፣ አቤል ዘበነ፣ ተስፋዬ እሸቱ እና ሌሎች ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 35 የሚደርስና በተለያየ ሙያ ላይ የተሰማሩት የቴዲ አድናቂ መደበኛ ጠያቂዎች “የቅዳሜና እሁድ” ጠያቂ የሚል ስም ወጥቶላቸው ነበር። ቴዲ ስለነዚህ ጠያቂዎች ሲያነሳም፤ “ቅዳሜና እሁድን ጠዋትም ከሰዓትም ያለመታከት ተመላልሰው ይጠይቁኝ ነበር። እነሱን ሳስብ ልክ አብረውኝ እንደታሰሩ ያህል እጨነቅ ነበር። ለነዚህ ወጣቶች እግዚያብሔር ብድራቸውን ይክፈላቸው” ብሎናል።

 

እናቱና ቤተሰቡ

ወ/ሮ ጥላዬ አራጌ (ራዬ) ልጇ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከታሰረ ጀምሮ ያሉትን ጊዜያት ሁሌም ጤናዋ ይታወክ ነበር። በተለይ በመጨረሻዎቹ የቴዲ የፍርድ ቤት የውሳኔ ቀጠሮ አካባቢ ከፊቷ ጀምሮ ተጐሳቁላ ነበር። በትናንትናው ዕለት ግን ፊቷ ፈክቷል። የለበሰችው ነጩ የአበሻ የሀገር ባህል ልብስ ውበቷን አጉልቶላታል።

 

“ደስታ ውበት ነው። ዛሬ እኔም ከቴዲዬ ጋራ አብሬ ተፈትቻለሁ። እግዚያብሔር ይመስገን! …፤ ከምንም በላይ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የዓለም ብድር ይግባው። የኔ ልጅ ብቻ አይደለም፤ የሁሉ ልጅ ነው፤ ‘እንኳን ደስ ያላችሁ!’ በይልኝ” ብላናለች።

 

“ቴዲዬ ግቢዬ ድረስ ነበር የመጣልኝ ሳገኘው ሰውነቴ ሁሉ ራደ፤ እየቆየሁ ስሄድ ነው እውነት መሆኑ የገባኝ። በዚህ አጋጣሚ የማረሚያ ቤቱ ሠራተኞች ከአስተዳደር ጀምሮ እስከታች ድረስ ላሉት ሠራተኞች እግዚያብሔር ይስጣችሁ! ዋጋ ከእግዚያብሔር ይከፈላልና ዋጋችሁን እግዚያብሔር ይክፈል! በእናንተ ተደስቻለሁ። ቴዲ የናንተም ልጅ ነው” ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።

 

የ70 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የእናቱ እናት፤ አያቱ ወ/ሮ አሰናቀች ታፈሰ በዕድሜ ብዛት ተዳክመዋል፤ ነገር ግን ዱላቸውን ተመርኩዘው ደስታቸውን ወዲያና ወዲህ እያሉ ይገልፃሉ። “መታሰሩን ስሰማ የተሰማኝን ኀዘን እንዲህ ነው ብዬ ለመግለጽ አቅም የለኝም። ነገር ግን ሁሌም በፀሎት ፈጣሪዬን ስለማመን ቆይቻለሁ። እዚች ቤት መታሰሩን እንደሰማሁ፤ እዚችው መፈታቱን ስሰማም ደስታዬን የምገልጽበት ቋንቋ አጥሮኛል። በዚህ አጋጣሚም ከቤተሰቡ እኩል ሲጨነቅለት የነበረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደስታውም የሱ ነውና እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ” በማለት ምስጋናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

 

ከሀገር ፍቅር ትያትር ቤት መድረክ በስተጀርባ

አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል፤ ለአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ጅማሮ የመጀመሪያዋ አጋር መሆኗ ይነገርላታል። በፍርድ ቤት ቀጠሮዎቹና በአንድ ዓመት ከአራት ወር የእስር ቆይታው አንዲት ቅዳሜን ከእስር ቤት ቀርታ አታውቅም። የመፈታቱ ዜና በተሰማበት በዚያች ሰዓት ግን በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት አዳራሽ ለተገኘው ተመልካች “ሩብ ጉዳይ” የተሰኘውን ትያትር ለማሳየት ከመድረኩ ጀርባ ትጠባበቃለች።

 

“ከጠዋት ጀምሮ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ከቤቴ ሳልወጣ የቴዲን መፈታት ስጠባበቅ ነበር። ከሰዓት ወደትያትር ቤት ሄጄ ከጓደኞቹ ጋር ስደዋወል ፍርድ ቤት መፈቻ እንደፃፈለት ሰምቼ ፈነደኩ። ትያትሩን ለመጀመር 15 ደቂቃዎች ያህል ሲቀሩኝ ደግሞ የመፈታቱን ዜና በስልክ ሰማሁ። ደስታዬን መግለጽ አቃተኝ። ከመድረኩ ጀርባ በደስታ ቀለጠ። ከዛ በኋላ ትያትሩን በጥሩ ሁኔታ አጠናቀቅኩ። አብረውኝ የሚሠሩ በሙሉ፤ ‘እንዲህ እንድትሠሪ ሁሌም ስለ ቴዲ ጥሩ ዜና መስማት አለብሽ ማለት ነው?’ ሲሉም ቀለዱብኝ።” ብላለች።

 

በርካታ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ ደስታቸውን የገለፁ ሲሆን፤ ቤተሰቦቹና አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ጉዳዩን ጉዳዩ አድርጐ ሲጨነቅ ለነበረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ “እንኳን ደስ አላችሁ! እግዚያብሔር ብድራችሁን ይክፈላችሁ!!!” የሚል መልዕክት እንድናስተላልፍላቸው ወትውተውናል።

 

 

ተያያዥ

 Copyright © 2008 - 2009 EthiopiaZare.com. All Rights Reserved.

Make a Free Website with Yola.